
ቂርቆስ
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አለባቸው አሞኜ በዛሬው ዕለት በቢሮአቸው ቁጭ ብለው የህዝብ አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት ከአንድ ተገልጋይ በደረሰባቸው ጥቃት ህይወታቸው አልፏል።
ከግል ጉዳዩ ጋር በተያያዘ የወረዳ ስራ አስፈፃሚውን የገደለ የፖሊስ አባል በቁጥጥር ሥር መዋላችን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወረዳ 8 ዋና ስራ አስፈፃሚ የእለት ከእለት ተግባራቸውን በማከናወን ላይ እንዳሉ ዛሬ፣ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ/ም ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት ላይ በፖሊስ አባል ተገድለዋል፡፡
ግድያውን የፈፀመው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የካሳንቺስ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት የቀጠና ኦፊሰር የሆነ አባል የግል ጉዳዩ እንዲፈፀምለት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለወረዳ 8 አስተዳደር ጽ/ቤት ያመለክታል፡፡
ወረዳው ጉዳዩን ተመልክቶ ምላሽ እንደሚሰጠው የተገለፀለት ቢሆንም ጥያቄዬ እንዳይፈፀም የከለከልከው አንተነህ በሚል ምክንያት የወረዳውን ዋና ስራ አስፈፃሚ ቢሯቸው ውስጥ በስራ ላይ እንዳሉ በታጠቀው ሽጉጥ መግደሉ ታውቋል፡፡
ወንጀሉን የፈፀመው የፖሊስ አባል በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራው እየተጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ፍትህን ለማረጋገጥ የሚያከናውነውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፆ የፖሊስ አባሉ በፈፀመው ድርጊት ማዘኑን በመግለፅ ለሟች ቤተሰቦች ፣ ጓደኞችና የስራ ባልደረቦች መፅናናትን ተመኝቷል፡፡ (የአገር ቤት ድምፅ – ጌጡ ተመስገን)
