
የኢትዮጵያ የመሬት ምልከታ ሳ ተላይት አገልግሎት ላይ በመዋሉ በየዓመቱ ለሳተላይት መረጃ ይወጣ የነበረውን 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ማስቀረቱን የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት የምህንድስና ዲዛይን የሚሰራበትን ሂደት የሚያሳይ መጽሐፍና የሳተላይት መተግበሪያ ይፋ አድርጓል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ፤ የኢትዮጵያን የቆዳ ስፋት የሚሸፍን 2 ሜትር የሳተላይት ጥራት(ሪዞሉሽን) ያለው መረጃ እንደ አገር እየተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ በዓመት ለሳተላይት መረጃ ስታወጣ የነበረውን 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር አስቀርቷል ብለዋል።
የሳተላይት መረጃ ለተፈጥሮ ኃብት አስተዳደር፣ የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማትና ለተረጋገጡ መረጃዎች የላቀ ጠቀሜታ እንዳለውም አስረድተዋል።
የሳተላይት መረጃዎች የተፈጥሮ አደጋን ቀድሞ ለመከላከልና ወቅታዊ መረጃዎችን በማግኘት ለአገር ልማትና እድገት ያለውን አስተዋጽዖም ጠቅሰዋል።
በታኅሳስ 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያውን “ኢቲ አር ኤስ ኤስ-01” የመሬት ምልከታ ሳተላይት ከቻይና የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ወደ ሕዋ መላኳ ይታወሳል።
በታኅሳስ 2013 ዓ.ም ደግሞ “ኢቲ-ስማርት-አር ኤስ ኤስ” የተሰኘችውን ሁለተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በተመሳሳይ አምጥቃለች።
ሁለቱም ሳተላይቶች ግብርና፣ የመሬት አስተዳደር፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የተፈጥሯዊ አደጋዎችና ሌሎች ተጓዳኝ መረጃዎችን ተደራሽ የሚያደርጉ መሆኑ ይታወቃል።
የምህንድስና ዲዛይን የሚሰራበትን ሂደት ለማሳየት ይጠቅማል በሚል የተዘጋጀው መጽሐፍ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
