
በዓለም ደረጃ ከ 140 ሺ በላይ የታወቁ የእንጉዳይ ዝርያዎች አሉ። ከነዚህም መካከል ከሁለት ሺህ የሚበልጡት የእንጉዳይ ዝርያዎች ለምግብነት እየዋሉ ሲሆን ወደ አንድ ሺ የሚደርሱት ዝርያዎች ደግሞ በ80 ሀገራት ውስጥ በኢንዱስትሪ ደረጃ እየተመረቱ ለምግብነትና ለገቢ ምንጭነት እየዋሉ ይገኛሉ። ከ650 በላይ የሚሆኑ የእንጉዳይ ዝርያዎች ደግሞ በተለያዩ አገራት ለመድኃኒትነት እየዋሉ ናቸው።
ኢትዮጵያ ባላት የሥርዓተ ምህዳር ተለያይነት አማካኝነት ልክ እንደ እንስሳትና እጽዋት ብዝሀ ሕይወት ዝርያዎች በርካታ አይነት የእንጉዳይ ዝርያዎችንም ይዛለች። እስካሁን በኢትዮጵያ የእንጉዳይ ዝርያ አሰሳ እና ቅኝት ተደርጎ የተጠናቀቀ ባይሆንም እስካሁን ግን 60 የሚደርሱ የእንጉዳይ ዝርያዎች ተመዝግበው ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል 25 የሚሆኑት ዝርያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ለምግብነትና ለመድኃኒትነት እየዋሉ ነው።
እንጉዳይ በተለያየ ሥርዓተ ምህዳር በዋናነት በጫካ፣ ዛፍ ላይ፣ የግጦሽ መሬት፣ በእርሻ መሬትና፣ የምስጥ ኩይሳ ላይ የሚበቅል ሲሆን በሁለት ይከፈላል። እነሱም የሚበሉ (Edible) እና መርዛማ (toxic) የእንጉዳይ ዝርያዎች ናቸው። መርዛማ እና የሚበሉ ሰለመሆናቸውም ተለይቶ የሚታወቀውም በባለሙያ ድጋፍ ወይም እንጉዳይን ለረጅም ጊዜ የመሰብሰብና የመጠቀም ልምድ ባላቸው ሰዎች ብቻ ነው።
እንጉዳይ በተፈጥሮ በጫካ በቅሎ የሚገኝ (wild mushroom) ወይም ደግሞ ሰዎች በቤተ ሙከራ የሚያሳድጉ ወይንም ደግሞ በቤታቸው የሚያመርቱ (Cultivated mushroom) ሲሆን አካባቢን የጫካ እንጉዳይ ዝርያዎች (Wild mushroom species) የሚበክሉና በቀላሉ መበላት የማይችሉ ቆሻሻዎችን (Cellulose, Lignin, Hemicellulose) በመሰባበር ለእድገታችው ይጠቀማሉ። በዚህም የእድገታቸው ሂደት አካባቢን ከብክለት ይከላከላሉ።
እንቦጭ እፅዋትን በምግብነት የሚጠቀም መሆኑ ልዩ ባህሪው ሲሆን ከዚህ ጋር በተያያዘም እንቦጭን በመመገብ ማጥፋት የሚችል የእንጉዳይ ዝርያ በምርምር ስለመገኘቱ የኢትዮጵያ ደን ልማት ማስታወቁ ይታወሳል። እንጉዳይ ለሰው ልጆች በምግብነት የሚውል በመሆኑ ጠቃሚ ያልሆኑ እንደ እንቦጭ ያሉ አረሞችንም ለማጥፋት በአማራጭነት ይጠቀሳል።
የእንጉዳይ ዝርያዎች ለምግብነት ከመዋላቸውና አካባቢን ከብክለት ከመጠበቃቸው በተጨማሪ የደንና የስነ-ምህዳርን ጤንነት ለመጠበቅ አገልግሎት ይሰጣሉ። በተለይም እንደ አማኒታሲዬ (Amanitaceae)፣ ሩሱላሴ (Russulaceae)፣ ቦሌታሴ (Boletaceae)ና ካንታሬላሴ (Cantharellacea) ያሉ የእንጉዳይ ዝርያዎች ከእፅዋት ሥር ጋር ትስስር በመፍጠር እፅዋቱ ብዙ ማዕድን እንዲያገኝና ድርቅን መቋቋም እንዲችልም ያደርጋሉ።
እንጉዳይን የተለያዩ ቆሻሻዎችን በመጠቀም በቤት ውስጥ ማምረቱ በሀገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ላለው የህዝብ ቁጥር ዘላቂነት ያለው የምግብ ምንጭ የሚሆንና ኢኮኖሚን መደገፍ የሚችል አንዱ መንገድ ነው። እንጉዳይ እንደ ፕሮቲን፣ ካርቦ ሀይድሬት፣ ሚኒራል፣ ቫይታሚን፣ ፋይበር እና ውሃ ያሉ አስፈላጊ ንጥረ-ነገሮችን የያዘ ነው። ስለሆነም እንጉዳይ ለምግብነት፣ ለጤና (ለመድኃነትነት)፣ ለገቢ ምንጭነት እንዲሁም አካባቢን ከብክለት ለመከላከል ያገለግላል።
ሰዎች እንጉዳይን ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ እንደሚጠቀሙ የተለያዩ መዛግብቶች ያስረዳሉ። አሁንም በደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እንጉዳይን ከጫካና ከእርሻ መሬት በመሰብሰብ እየተጠቀሙ ይገኛሉ። እንጉዳይ በተለያየ ስነ-ምህዳር ያለው ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል። ለዚህም የደን መጨፍጨፍ፤ የአየር ንብረት ለውጥ፤ ሳይንሳዊ ያልሆነ የኬሚካል አጠቃቀም እና የመሬት መራቆት እንዲሁም እንጉዳይን የተመለከተ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዘዴ አለመኖር ያሉ ምክንያቶች በዋናነት ለእንጉዳይ ዝርያ መቀነስና መጥፍት ተጠቃሽ ናቸው።
እንደ ሀገር ኢትዮጵያ በጣም ብዙ የእንጉዳይ ዝርያዎች እንዳሏት ቢታመንም እስካሁን ግን ፍለጋው ተጠናቆ አገሪቱ እንዳላት የእንጉዳይ ሀብት መጠን በሚፈለገው መጠን ተጠቃሚ አልሆነችም። በኢትዮጵያ ብዝሀ-ሕይወት ኢንስቲትዩት በደቂቅ አካላት ብዝሀ ሕይወት ዳይሬክቶሬት በፈንገስ ብዝሀ ሕይወት ኬዝ ቲም በአራት የእንጉዳይ ዝርያዎች ማለትም (Pleurotus ostreatus, pleurotus sajor-caju, Shiitake እና አንድ የጫካ እንጉዳይ) ለቀጣይ ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት በተለያዩ የኢንዱስትሪና የግብርና ቆሻሻን በመጠቀም የምርምር ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
