በአሉቶ ላንጋኖ የከርሰምድር እንፋሎት ፕሮጀክት ከተቆፈሩት 10 የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ጉድጓዶች መካከል የስድስት ጉድጓዶች ቁፋሮ ተጠናቆ የምርት ሙከራ ሥራ መከናወኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጂኦተርማል ሴክተር ልማት ፕሮጀክት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ መሳይ ፈቃዱ እንደተናገሩት የቀሪ አራት ጉድጓዶች የሙከራ ሥራ እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው፡፡
የአራት ተጨማሪ ጉድጓዶች ቁፋሮ ለማከናወን ከዓለም ባንክ ጋር ስምምነት ላይ በመደረሱ የፕሮጀክቱ ሥራ እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም መራዘሙን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
የምርት ሙከራ ከተከናወነባቸው ስድስት ጉድጓዶች 25 ሜጋ ዋት ኃይል መገኘቱንም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ከዓለም ባንክ በብድር በተገኘ 143 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እየተከናወነ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 24 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላሩ በድጋፍ የተገኘ መሆኑንም ነው ዳይሬክተሩ የገለፁት፡፡
የእንፋሎት ኃይል ግንባታ ዘርፍ በሀገራችን አዲስ እንደመሆኑ ከፕሮጀክቱ ባሻገር በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን የገለፁት አቶ መሳይ የተቋሙ ባለሙያዎች በሥራ ላይ ስልጠና ተጨባጭ እውቀት እና ክህሎት ማግኘታቸውን አብራርተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለ110 ኢትዮጵያዊያን ቋሚ፣ ለ40 ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡
በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ 70 ሜጋ ዋት ለማመንጨት የታለመ ሲሆን የመጀመሪያ ምዕራፍ 35 ሜጋ ዋት ከተከናወነ በኋላ ሁለተኛው ምዕራፍ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
