
በመኮንን ተሾመ (የሚዲያ ባለሞያና የጨቅላ ህፃናት እድገት ተግባቦት አማካሪ)
ይህ ፅሁፌን ለመፃፍ ያነሳሳኝ ባለፈዉ እሁድ በኢ∙ቢ∙ኤስ ቴሌቪዢን በ”ሰይፉ በኢ∙ቢ∙ኤስ” ፕሮግራም ላይ ተወዳጁ ኮሜዲያን እሸቱ መሰለ እንግዳ በሆነበት ጊዜ የተላለፈዉ የተዛባ መረጃ ነዉ ( 👉 https://youtu.be/ZTiF2W54plE?si=tN6HNom0VyncFDbA ) ።
በወቅቱ በተላለፈዉ የቴሌቪዢን ፕሮግራም ኮሜዲያን እሸቱ ፍፁም ቅንነትና ቁጭት በተሞላበት መልኩ በሌላ ጉዳይ ላይ በተለየ መልእክተኛ “አምባሳደር” ∕Messenger⁄ መሆን እንደማይፈልግ ገልፆ በህፃናት መቀንጨር (Stunting) ላይ ግን መልእክት እንዳለዉ በመግለፅ በመቀንጨር ዙሪያ የተወሰኑ ሃሳቦችን አስተላልፉአል።
ኮሜዲያን እሸቱ የየትኛዉ ድርጅት መልእክተኛ “አምባሳደር” እንደሆነ ባላዉቅም በወቅቱ የአረንጓዴ ጉርሻ / የ”ግሪን ጉርሻ” የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ መጀመሩን ጠቅሶ ዘመቻዉም “ከጎመን እና አትክልት” መመገብ ጋር የተገናኘ መሆኑንና የመቀንጨር ችግር ሙሉ በሙሉ ጎመን እና አትክልት ካለመመገበ ጋር የሚመጣ ችግር መሆኑን አስረግጦ ለኢትዮጵያ ህዝብ በአፅንኦት አሳስቦ ይህንንም ሀሳብ ይበልጥ ለማፅናት የፕሮግራሙን አዘጋጅ አቶ ሰይፉ ፋንታሁንን የፆም ምግብ በማቅረብ ከምግቡ ላይ ጎመን በማጉረስ እና በመጉረስ የጎመንን የመቀንጨር ፍቱን መድሃኒትነት ለህዝባችን ለማስተማር ጥረት አድረጓል።
ይሁንና እኔ በጉዳዩ ዙሪያ ለረጅም ጊዜ እንደሰራ የተግባቦት (Communication) ባለሞያ ኮሜዲያን እሸቱ ያሰተላለፈዉ የቅንነት መልእክት ለህዝባችን ሲባል እና ጉዳዩ ካለዉ ክብደት አንፃር መሰተካከል እንዳለበት በማመን ይሀንን መጣጥፍ አዘጋጅቻለሁ።
አረንጓዴ ጉርሻ ⁄ “ግሪን ጉርሻ” ⁄ወይስ “ምጥን” ጉርሻ ?
የአትክልት በሽታን የመከላከል ጠቀሜታ እንዳለ ሆኖ ከእንሰሳትና የእንስሳት ውጤቶች የሚገኘው ኘሮቲን ደግሞ ለጨቅላ ህፃናት አካላዊና የአንጎል (brain) ክፍል እድገት እጅግ ወሳኝ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

ከሳይንስ እና በዘርፉ ከተደረጉ ሰፊ ጥናቶች መረዳት እንደምንችለዉ የመቀንጨር (Stunting) ችግር “ከጎመን እና አትክልት” ጋር ብቻ ሳይሆን ከሁሉም የምግብ አይነቶች ( ከሀይል ሰጪ ፣ከበሽታ ተከላካይና በተለይም ከገንቢ⁄በልዩ ሁሌታ ከእንስሳት ፕሮቲን እጥረት) እንጂ ከጎመን ወይም ከአትክልት እጥረት ብቻ የሚከሰት አለመሆኑን ይልቁንም ከእንስሳት ፕሮቲን እጥረት እነደሆነ በመረዳት የሚተላለፈዉን መልእክት ማስተካከልና ማረም እነደሚገባ መታወቅ ይኖርበታል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የመቀንጨርን ችግር ለመከላከል በባለሞያዎች ከሚመከሩ ምግቦች መካከል በፕሮቲን ይዘታቸዉ የበለፀጉ እንደሆኑ እንረዳለን።
ከእንስሳትና ከወተት ውጤቶች ፣ እንቁላል ፣ ዓሳ ፣ እርጎ ፣ የዶሮ ሥጋ እንዲሁም ከእፅዋትና ጥራጥሬ ፕሮቲን ደግሞ እንደ ለውዝ ፣ የቤሪ ፍሬዎች እና አቮካዶ በዋነኝነተ የሚጠቀሱ ናቸዉ።
ስለዚህ መቀንጨርን (Stunting) ለመከላከል የሚያስፈልገዉ የአመጋገብ ሁኔታ ከሁሉም የምግብ አይነቶች ( ከሀይል ሰጪ ፣ ከበሽታ ተከላካይና በተለይም ከገንቢ⁄በልዩ ሁኔታ ከእንስሳት ፕሮቲን) ላይ ያተኮረ መሆኑን በመረዳት ኮሜዲያን እሸቱ መልእክቱን አረንጓዴ ጉርሻ የ”ግሪን ጉርሻ” ሳይሆን “ምጥን ጉርሻ” ቢለዉ የኔ ምክር ነዉ።
የመቀንጨር ዋና ዋና ምክንያቶች
በመሰረቱ መቀንጨር (Stunting) በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ሳቢያ የሚከሰት የአካልና የአይምሮ (በጨቅላ ህፃንነት ወቅት የአንጎል እድገትና መዳበር ችግር) እድገቶች መገታት ሲሆን ይህም አብዛኛውን ጊዜ በልጅነት ጊዜ በተለይም በመጀመሪያዎቹ 1,000 ቀናት ውስጥ በተላይም ከተፀነሱ ጀምሮ እስከ ሁለት አመት ድረስ ካለ የአመጋገብና የጤና እንክብካቤ እና ሌሎች እንክብካቢዎች ጋር የሚያያዝ ነዉ።
ይህም በህፃናት አመጋገብ ፣ በሽታ የመከላከል ስርዓትን ፣ የመማር ችሎታን እና እንዲሁም በአዋቂነት ጊዜም የሚኖርን ምርታማነትን ሁሌታ ይጨምራል።
በእርግዝና ወቅት ጨምሮ በጨቅላ ህፃንነት ወቅት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ፣ የንፅህና አጠባበቅ እና የጤና ጉድለቶች ጋርም ይያያዛል።
ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች
በእርግዝና ወቅት የእናቶች አመጋገብ ሁኔታ
በሕፃናት ላይ የጤና ተጽእኖ
በአራስ ሕፃናት ላይ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት
ከትዉልድ ወደ ትዉልድ የሚተላለፍ (የጄኔቲክ) እና የሆርሞን ምክንያቶች
ከንጹህ ውሃ አቅርቦት ጋር የተገናኙ ችግሮችም ሊጠቀሱ ይችላሉ።
በተጨማሪም መቀንጨርን ስናስብ የቁመት ማጠርን ብቻ ሳይሆን የአካልም የአንጎልም እድገት ችግር መሆኑን ፣ አንድ ጊዜ ከተከሰተ በምንም አይነት ሁኔታ ሊቀየር የማይችል (Irreversible) የሆነ የጤና ችግር መሆኑን ፣ አንዳንድ ጊዜም ችግሩ የበረታ ከሆነ ከትዉልድ ወደ ትዉልድ የሚተላለፍ መሆኑን ፣ በተለይም ከእንስሳት ፕሮቲን እጥረት የሚከሰት መሆኑን ማስተዋል ያሰፈልጋል።
ሌላው ከመቀንጨር ጋር ተያይዞ በሀገራችን በስፋት ያለ ችግር መሆኑ ቢታወቅም በወቅቱ በቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ላይ የተጠቀሰው ምጣኔ 50% እና 39% ተብሎ የተጠቀሰው አሀዝ አሁን ካለው የመረጃ ክፍተት አንፃርና የቆዩ ጥናቶች ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ በደንብ መታየት ይኖርባቸዋል። ከቅንጨራ ምጣኔ ጋር በተያያዘም ከክልል ክልልም የተለያየ መሆኑንም መገንዘብ ይገባናል። በመሆኑም “መልእክተኛ አምባሳደሮች” ቁጥርና ስታትስቲክስ ሲናገሩ በደንብ የተጣራና ወቅታዊ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።
ለመጀመሪያዎቹ 1000 ቀናት ትኩረት መስጠት⁄የመቀንጨር ፍቱን መፍትሄዎች
ስለዚህ ይህንን የጤና ፣ የማህበራዊና የወደፊት የሀገር የእድገት ችግር የሆነዉን የመቀንጨር (Stunting) ሀገራዊ ችግር ለመቅረፍ ሁሉም የሚመለከታቸዉ አካላት
1 – በእርግዝና ወቅት ለእናቶች የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ /Maternal Nutrition/
2 – ከ 0-6 ወር እድሜ ድረስ (ለጨቅላ ህፃናት ጡት ብቻ ማጥባት) /Exclusive Breast Feeding/
3 – ከ6 ወር እስከ 2 አመት እድሜ – ተጨማሪ ምግብ/Supplementary Feeding/ ( ከሀይል ሰጪ ፣ከበሽታ ተከላካይና በተለይም ከገንቢ ምግቦች ⁄በልዩ ሁሌታ ከእንስሳት ፕሮቲን እጥረት ፣ የተፈጨ ቋንጣ ፣ የተወሰነ እንቁላል የህፃናት ምግብ ላይ በመጨመር) ቅንጨራን የመከላከል ስራ መስራት ይኖርባቸዋል።
ስለዚህ ጉዳዩ ካለዉ ክብደት አንፃር ህዝባችን እንዳይደናገር ኮሜዲያን እሸቱም በዚሁ መሰረት የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻውን መልእት ቢያስተካክለዉ የሚል ምክሬን መለገስ እፈልጋለሁ።
