
መኮንን ተሾመ – / አዳማ /
(አዳማ ፣ ኢትዮጵያ ፣ ጥር 17፣ 2017 ዓ.ም. ) ፣ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዛሬ በአዳማ ከተማ በተደረገዉ ያለፈዉን የበጋ ወቅት ትንበያ ግምገማና እና በመጪወቹ አራት ወራት ማለትም ከካቲት እሰከ ግንቦት 2017 ዓ.ም. ያለዉን ደግሞ የበልግ ወቅት የአየር ጠባይ ትንበያ ይፋ ባደረገበት ወቅት እንደገለፀዉ የበልግ ወቅት ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸዉ በሆኑት በደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ እንደሚኖራቸዉ ይፋ አድርጓል።
በዚሁ መሰረት፣
- በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸዉ በሆኑት የሶማሌ ክልል ደቡባዊ ክፍል መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል ፣
- የቦረናና ጉጂ ዞኖች, የሲዳማ የማዕከላዊና የደቡብ ኢትዮጵያ መደበኛና ከመደበኛ በላይ፤
- የደቡብ ትግራይ፡ የምስራቅ አማራ፤ አፋር፣ መካከለኛው እና የምስራቅ የሀገሪቱ አከባቢዎች ላይ መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል ፣
- የምዕራብና የደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አከባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው በማብራሪያው ተመላክቷል ፣
- በተጨማሪም የምዕራብ እማራና የጥቂት የቤንሻንጉልጉሙዝ ሰሜናዊ ክፍል እልፎ አልፎ ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት ዝናብ እንደሚያገኙ ተነግሯል ፣

የዘንድሮዉ የበልግ ትንበያን ይፋ ለማድረግ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎችና ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት እነዚህን ትንበያዎች ይፋ ያደረጉት የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሳምነዉ ተሾመ እንዳሳሰቡት በትንበያዉ መሰረት ህበረተሰቡ እንደየ አካባቢዉና የዝናቡ መጠን አስፈላጊዉን እርምጃ መዉሰድ ይገባዋል።
“ዝናብ አጠር በሆኑት አከባቢዎች በየዕለቱ የሚኖረውን የዝናብ ዉሃ በአግባቡ በመሰብሰብ በቁጠባና በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል።” ብለዋል።
”በአንፃሩም አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት ተደጋጋሚነት ያለው ከባድ ዝናብ የሚኖር ሲሆንና፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑት ረባዳማና የወንዝ ዳር እንዲሁም በከተሞች አካባቢዎች የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አለታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ እንዲያቻል አስፈላጊዉን የጥንቃቄ ስራ ከወዲሁ መስራት ያስፈልጋል፡፡” ሲሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር አሳምነዉ ጠቁመዋል።

እሳቸዉ እንዳሉት ህብረተሰቡ በሚቀጥለው የበልግ ወቅት የሚጠበቀውን የአየር ጠባይ ትንበያን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባትና የሚገኘውን የዝናብ መጠንና ስርጭት በእግባቡ በመጠቀም በዚህ ወቅት የሚካሄደውን የግብርና እንቅስቃሴ እና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎችን ከባለሙያዎች ጋር በመመካከር ማከናወን ያስፈልጋል።
ከሚኖረዉ የዝናብ ሁኔታም በተጨማሪ በአብዛኛዉ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከመደበኛዉ አንፃራዊ መጨመር እንደሚኖረዉም መተንበዩን ዶ/ር አሳምነዉ ይፋ አድረገዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር እና በዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ፕሬዝዳንት ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸዉ እንዳሉት የተሰጠዉ ወቅታዊ የአየር ሁኔታ ትንበያ በቀጣዩ 2017 ዓ.ም በልግ ወቅት፣ ሊኖር የሚችለውን የአየር ሁኔታ አስቀድሞ በመተንበይ ሊፈጠሩ የሚችሉትን ጎጂ ክስተቶች በመገንዘብ ተጽዕኖውን ለመቀነስ የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አክለዉም ኅብረተሰቡ በኢንስቲትዩቱ የሚሰጠውን ትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ በሚገባ እንዲከታተልና ጥቅም ላይ ማዋል ይገባዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ እነደጠቆሙት ኢንስቲትዩቱ በአዋጅ የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር በአግባቡ ለመወጣት ከአየር ሁኔታና ጠባይ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የተፈጥሮ አደጋዎች አስቀድሞ መከላከል እንዲቻልና ቅድመ ዝግጅትን በማጠናከር የአገሪቱን ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ በደንበኞች ፍላጎት የተመሰረተ አገልግሎት እየሰጠ ነዉ።
ኢንስቲትዩቱ የበጋ ወቅት ትንበያ ግምገማና መጪ በልግ ትንበያ ይፋ ለማድረግ ያዘጋጀውን መድረክ በንግግር የከፈቱት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሃብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃም አዱኛ ባስተላለፉት መልዕክት ኢንስቲትዩቱ ተግባርና ኃላፊነቱን በተሻለ ሁኔታ ለመወጣት ከልማት አጋሮች ጋር በቅርበት በመሥራት የማስፈጸም አቅሙን ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የዘንድሮ የበልግ ወቅት ትንበያ በተለይ ለበልግ አብቃይ ለሆኑ የአገራችን አካባቢዎች ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ የአደጋ ተጋላጭነትን በመቀነስ በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ አሳስበው ኢትዮጵያ ለጀመረችው ሁሉን አቀፍ የልማት እንቅስቃሴ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪቸውን አቅርበዋል።
በወቅቱ እንደተገለፀዉ ካሉ አለምአቀፍ እስተቶች መሃል በሀገራችን ለሚኖረዉ የአየር ጠባይ በተለይም መጪው በልግ አሁን በትሮፒካል ፓስፊክ ውቅያኖስ የባህር ወለል መቀት ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ (ENSO-Neutral) እንደሚሆን እንዲሁም የሰሜናዊ ህንድ ውቅያኖስ መደበኛ የባህር ወለል ሙቀት መጠን (NeutralHOD) ሆኖ ሊቆይ እንደሚችል የትንበያ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ማብራርያ ተሰጥቷል፡፡
ይህም የወቅቱ ዝናብ አጀማመር በአንዳንድ አከባቢዎች ላይ ቀድሞ እንዲጀምርና በአወጣጥ ረገድ ግን ዘግይቶ እንዲወጣ ሊያደርግ እንደሚችል የተገለፀ ሲሆን፤ በበልግ ወቅት ተደጋጋሚነት ያለው ደረቅ ሰሞናት ሊኖር እንደሚችልም ትንበያ ተሰጥቷል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ ባስተላለፉት መልእክ ኢንስቲትዩቱ በዘንድሮው የበጋ ወቅት ትንበያው ሊፈጠር የሚችለውን የዓየር ሁኔታ በጊዜና በቦታ ያለውን ስርጭትና ተጽዕኖን በተመለከተ ነሃሴ ወር 2016 ዓ.ም የወቅት ትንበያ ሰጥቶ እንደነበር እና ትንበያውም ከተከሰተው ጋር በአብዛኛው የተጣጠመ እና ተመሳሳይነት እደነበረው ጠቁመዋል፡፡
ይህም በአሁኑ ወቅት ኢንስቲትዩቱ የሚሰጡ የአየር ጠባይ ትንበያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ ፣ በአለም ላይ ካሉ አጋር አካለት ጋር በመተባበር እና በማነፃፀር የሚተነተኑ ሲሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስተማማኝነታቸዉ እየጨመረ መምጣታቸዉን የሚያሳይ መሆኑን አንስተዋል።
