
የውሃ አካሎቻችንን የዳርቻ ርቀት
By African Demystifier
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሕግ ከተሰጡት ኃላፊነቶች አንዱ በሀገሪቱ የውሃ አካላትን መንከባከብና ደኅንነታቸውን መጠበቅ ነው:: በአዋጅ 1263/2014 አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1/ሐ) ስር በተገለጸው መሠረት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተፋሰሶችን ከብከለትና ከጉዳት ለማዳን ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች በጥናት ይለያል፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይተገብራል፤ የውሃ አካላትና ተያያዥነት ያላቸው ሥነ ምህዳሮችን ይንከባከባል፤ ያስተዳድራል ተብሎ በግልጽ ተደንግጓል::
በዚህ መሠረት የውሃ አካላትን ደኅንነት ለመጠበቅ ተቋሙ በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በተመረጡ አካባቢዎች በሰፊው ባለፉት ዓመታት የተፋሰስ ሥራዎችን የተሠራ ሲሆን አሁንም በመሥራት ላይ ይገኛል:: ሥራዎቹን ውጤታማ ለማድረግ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን እና ሕጎችንም እያመነጨ ሲሆን በቅርቡ የተዘጋጀው የውሃ አካላት ዳርቻ ርቀትን የሚወስን ረቂቅ አዋጅ አንዱ ነው፡፡
የውሃ አካላትን ዳርቻ ርቀት የሚወስን አዋጅ የውሀ አካላት የምንላቸውን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሐይቆች፣ ወንዞች፣ ኩሬዎች፣ ምንጮች፣ ወንዞች የከርሰ ምድር ውሃን ጨምሮ ረግረጋማ መሬቶችን ሥነ ሕይወታዊና ሥነ ምህዳራዊ ጥበቃ ለማድረግ፣ ለመንከባከብና ለመጠበቅ የሚወጣ አዋጅ ነው፡፡

“የውሃ አካላትን ከብክለትና ከብክነት መጠበቅ ለአፍታም ቢሆን ቸል ሊባል የማይገባው ተግባር ነው::” ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ
ይህን ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀት ያስፈለገበት አንዱና ወሳኙ ምክንያት የውሃ አካል ዳርቻ ሥርዓተ ምህዳር ወደ ሌላ መሬት አጠቃቀም በመቀየሩ ምክንያት ከመጠን ያለፈ ደለልና ንጥረ ነገሮች ወደ ውሀ አካሉ በመግባት በውሃው መጠን፣ ጥራትና ብዝን ሕይወት እና ተያያዥነት ባለው የሥርዓተ ምህዳር አገልግሎት ላይ ችግር እየተከሰተ በመምጣቱ፣ በሕግ አግባብ ክልከላዎችን በማስቀመጥ የውሃ አካላቱን መታደግ አስፈላጊ በመሆኑ ምክንያት ረቂቅ አዋጁን ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኗል፡፡
የውሃ አካላት ዳርቻን መወሰንና ማስከበር ለውሃ አካሉ _ ዘላቂነት፣ ውሃውን ከብክለትና ብክነት በመጠበቅ ሀብቱ በዘላቂነት እንዲጠቅም በማድረግ ረገድ ከፍ ያለ ጠቀሜታ አለው:: መረጃዎችን እንደሚያሳዩት የውሃ አካል ዳርቻ ባልተከበረበት ሁኔታ የውሃ አካሉ ደህንነት ሊረጋገጥ አይችልም፡፡
የውሃ አካላት ዳርቻ ርቀትን መወሰኛ አዋጅ በሀገሪቱ በሚገኙ በማንኛውም የውሃ አካል ላይ ተፈፃሚ የሚሆን አዋጅ ነው፡፡
የውሃ አካላት ዳርቻ አከላለል
ምንም እንኳን የውሃ አካላት ዳርቻ ርቀትን መወሰኛ አዋጅ የውሃ አካል ዳርቻ የሚለውን ቃል ብያኔ ባይሰጠውም ከአጠቃላይ የአዋጁ መንፈስ የምንረዳው አንድን የውሃ አካላት የሚያዋስን መሬት ማለት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ በዚህ አግባብ ረቂቅ አዋጁ የውሃ አካላት ዳርቻ አካላለልን በሚመለከት በሦስት ደረጃዎች ከፍሏቸዋል::
- የመጀመሪያው ፍፁም ጥብቅ፣
- ሁለተኛው ጥብቅ እና
- ሦስተኛው የቁጥጥር ዳርቻዎች በሚል በዝርዝር አስቀምጧቸዋል፡፡
በረቂቅ አዋጁ የተከለከሉና የተፈቀዱ ተግባራት ወይም ድርጊቶች
በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 11 ድንጋጌ መሠረት በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 4 መሠረት በተከለለ የውሃ አካላት ዳርቻ ማንኛውንም ድርጊት መፈጸም የተከለከለ መሆኑን ገልጾ የሚከተሉት ተግባራት ግን ከሚመለከታቸው አከላት ጋር የውሃ አካሉን ዳርቻ እና ሥርዓተ ምህዳር ላይ ሊደርስ የሚችል ጉዳትን መከላከል ስለሚቻልበት ሁኔታ በመመካከር ሊከናወኑ እንዲሚችሉ ይፈቅዳል፡፡ እነሱም
ሀ, የውሃ አካሉን _ ዳርቻ ሥርዓተ-ምህጻር ለመጠበቅና ለመንከባከብ የሚጠቅሙ እንደ ቁጥቋጦ፣ ዛፍ እና ሣር የመሳሰሉ እፅዋትን መትከል
ለ ጥናትና ምርምር ማካሄድ
ሐ. የጎርፍ መከላከል ሥራ
መ. ሃይማኖታዊ ወይም ባሕላዊ ሥርዓትን መፈጸም
ሠ. በከተማም ሆነ በገጠር ውስጥ በሚገኝ ጥብቅ የውሃ አካል ዳርቻ ውስጥ ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚውል መናፈሻ፣ ለእግረኛ እና ለብስክሌት አገልግሎት የሚውል መንገድ ሥራ፣
ረ, በገጠር በሚገኝ ጥብቅ የውሃ አካል ዳርቻ ውስጥ ለአካባቢው ህብረተሰብ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያስገኙ እንደ የፍራፍሬ ዛፍ ልማትን፣ ንብ ማነብን፣ ዘመናዊ አሳ እና አዞ እርባታን፣ ለከብት መኖ የሚውል ሳር አጭዶ መውሰድን የመሳሰሉ ተግባራትን፣
ሰ. በከተማ ወይም በገጠር የቁጥጥር የውሃ አካል ዳርቻ ውስጥ የኬሚካል ማዳበሪያዎችን፣ ፀረ ተባዮችንና ሌሎች ለውሃ ብክለት ምክንያት የሚሆኑ ግብአቶችን የማይጠቀም ግብርና ማከናወን ተቀምጧል፡፡ (የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር)
