
የሩሲያዊው ጠፈርተኛ ሰርጌ ሰቨርቺኮቭ በህዋ ሳይንስ ያካበተውን እውቀት እና ልምድ ለኢትዮጵያ ምሁራን፣ የዩኒቨርሲቲና ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በትላንትናዉ እለት በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት አጋርቷል።
የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀዉ የሩሲያን የህዋ ሳይንስ መልካም ልምድ መቅሰም የሚያስችል የልምድ ልውውጥ በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት ተካሂዷል።
ኢትዮጵያውያን የዘርፉ ምሁራን እና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በልምድ ልውውጡ ተካፍለዋል፡፡
የዩኒቨርሰቲው ፕሬዚዳንት ደረጄ እንግዳ (ዶ/ር) የልምድ ልውውጡ በተለይም ለተማሪዎች ከፍተኛ መነሳሳት ይፈጠራል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የሞስኮ ኢንጂነሪንግ ኢንስቲትዩትን ጨምሮ ከተለያዩ የሩሲያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
የልምድ ልውውጡ የእርስበርስ ግንኙነትንለማጠናከር እና ለጋራ ግብ ትልቅ አበርክቶ እንዳለውም አስገንዝበዋል፡፡

የስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኗ አስረድተዋል፡፡

ለተጀመረው ስራም የሩሲያ ልምድ እና አጋዥነት ከፍተኛ ሚና እደሚጫወት ተናግረዋል፡፡
የጠፈርተኛው ልምድ ማጋራትም ኢትዮጵያ ነገ በርካታ የህዋ ሳይንስ ተመራማሪ እንድታፈራ ያነቃቃል ብለዋል።
