
በጅንፎ ዱላ
በጓያ ዉስጥ ያለዉ መርዛማ ንጥረ ነገር ምንድን ነዉ ?
በመኮንን ተሾመ ቶሌራ
ሰሞኑን ስራ አመሻሽቼ ወደ ቤት እንደገባሁ ሁል ጊዜ ሳሎን ሶፋ ላይ ቁጭ ብላ የኔን መምጣት የምትጠባበቀዉ እናቴ ከጎረቤቶቻችን ጋር ‘ወግ’ ይዛ አገኘኋት።
መቼም የዉቢት ‘ወግ’ ስራዬ ብሎ ላዳመጠዉ ከየትኛዉም መብልና መጠጥ ይልቅ ጣዕም አለዉ። እናም በአጋጣሚ ስለ ጓያ ሽሮ አንስታ ስታወራ ጆሮዬን ጣል አድርጌ መስማት ጀመርኩ።
“ጓያ ተጠንቅቀዉ ካልያዙት እንደጥቅሙ ሁላ ጉዳቱም ከባድ ነዉ። መናጢ ነዉ። በርግጥ ጥቅሙም አያሌ ነዉ።” አለች።
“ምነዉ ‘ውቢት’ የእህል መናጢ አለዉ እንዴ? ጓያ ልክ እንደ አተረ፣ እንደ ባቄላ ፣ እንደ ምስር ያለ ምግብ ነዉ። እንደዉም እነዚህ ጥራጥሬዎች ስጋን ሁሉ በተወሰነ ደረጃ ተከተዉ ለሰዉነታችን ጥቅም የሚሰጡ በጣም ወሳኝ የምግብ ክፍሎች ናቸዉ። ዶክተሮች እንዲህ ሲሉ ሰልሰማሁም።” አልኳት። ትንሽ ፊደል መቁጠሬ ብልጭ ብሎብኝ ሀሳብ ለማስተካከል እየዳዳኝ።
“አንተ ደግሞ ሁል ጊዜ ማጣቀሻዎችህ ያንተ ዶክተሮች ናቸዉ። የነሱን ቃል የስላሴ ቃል ታደርገዋለህ። አትጃጃልብኝ።” ብላ ፈገግታ አሳይታይ ወጓን ቀጠለች።
“በጅንፎ ዱላ ብቻ ጠላቶቹን እየሰባበረ ጠመንጃ የሚቀማወን አጎቴን የሰባበረዉ ጓያ ነዉ።” አለችና ምሳሌ አቀረበች።
ጓያ ሰበረዉ ስለምትለዉ አጎቷ ጀግንነት በእርግጥ ብዙ ሰምቻለሁ። እናም ሁል ጊዜ ምነዉ በአካል ባወኩት ኖሮ እያልኩ እቆጫለሁ። ስለ ጀግንነቱ ከዘመዶቻችን ስሰማ ይገርመኛል። በተለይ የወይራና የክትክታ ጅንፎ ዱላዎቹን እንዴት እንደሚሰራና በዱላ ዎቹም ምን ተአምር እነደሚሰራ ብዙ ሰምቻለሁ።
ለዱላ የሚሆኑ ወይራና ክትክታ በሀገሩ እንደሱ የሚያዉቅ የሚመርጥ የለም ይላሉ። የወይራና ክትክታ ዘንጎችን መርጦ በእሳት እየለበለበ ማረቅ፣ አርቆ ቂቤ ማጠጣትና በጭስ እያስመታ እንዲጠነክር ማድረግ እናም በበሬ ወይም በፍየል ቆዳ ማስጌጥና ከታች ጫፉ ላይ የብረት ቀለበት/ጅንፎ/ በማስገባት ዱላዉ ሃይለኛ ምት የሚያሳርፍ እንዲሆን በማደረግ ማንም የሀገሬዉ ጎረምሳ አይስታካከለዉም ይላሉ።
እናም ይሄ ዉቢት “ጓያ አልመሸመሸዉ” የምትለዉ አጎቷ በሰላሙ ጊዜ ሲበዛ ቀልድ አዋቂና ተጫዋች፣ ያለውን ሲሰጥ የማይሳሳና ለሰዉ አዛኝም ነበር ይላሉ። ነገር ግን በዛዉ ልክ በርስት ፣ በሚስት ፣ በዘመድና በክብር የመጡበትን በርካታ ሰዎች እያቆሰለና እየገደለ ብዙ ጊዜ ይሸፍት ነበረ አሉ። በመጨረሻ ጓያ ጉድ ሰራዉ እነጅ።
ባላሰበዉ ጠላት በጓያ ከመሰበሩ በፊት ጉርምስናዉን ያሳለፈዉ ጠመንጃ በመወልወልና ጅንፎ ዱላ በመስራት ነበር።
ለምን ቢባል ለወንድ ልጅ ዱላ መያዝ በሀገሩ ባሕል በመሆኑ እንዲሁም ዱላዉ ከሰዉም ሆነ ከአዉሬ ጥቃት ለመከላከል ዋና መሳሪያ በመሆኑ ነዉ። በዛላ ላይ እሱ ደግሞ በዱላዉ ” ቅዘምዝም ” እየወረወረ ቆቅ እንኳን ሳይቀረዉ እያደነ ይገል ነበር ይሉታል።
እሱ ብዙ ጊዜ ተጨንቆና ተጠቦ በሚሰራዉ ጅንፎ ዱላዉ “ጠላቴ” ያለዉን ጭንቅላ/ቅንጥ/ መቶ ጠመንጃ ይነጥቅ ነበር ይሉታል። ወይም ለማሽላ መጠበቂያ በሰራዉ ወንጭፍ እንደ ዳዊት ሰዉ ያጠቃል ፣ ወይም ደግሞ ዘመናዊ መሳሪያ የያዙና ጠላቴ ያላቸዉን ሁላ እነሱ ሳያዩት በተራራ አናት ላይ በመውጣት እነሱ ከታች ሲያልፉ በ ‘መርግ’ ናዳ በማጥቃት ይማርክ ነበርም ይባላል። እናም ጀገና ወዳድ ዘመዶቹ ነብስ አጥፍቶም ቢሆን አሳልፈዉ ስለማይሰጡትና በዚያን ወቅት በነበረዉ ባህል መሰረት “ጉማዉንም” አዋተዉ ስለሚከፍሉለት እንደገና ህይወቱ ያጥላል።
እነዚህን የማጥታት ዘዴዎች ቀደም ካሉት ዘመዶቹ ሳያጠና አልቀረም። ጣሊያኖች ለወረራ በመጡ ጊዜና ‘የአላዉሃ- አላማጣ’ አስፋልት መንገድን በሀገሬዉ ጉልበት ሲያሰሩ የሱ ታላላቆች በተመሳሳይ መንገድ ጠላትን በድንገት ያጠቁ እንደነበረ ሳያጠና አልቀረም።
መቼም እሱና ዘመዶቹ ጥቃት አይግባቸዉ እንጅ ጠላት የታጠቀዉ ዘመናዊ መሳሪያ ለነሱ ቁብም አይደል። “ግንባሬን እንጅ ስሸሽ ጀርባዬን ተመትቼ ከወደኩ አትቅበሩኝ። አሞራ ይብላኝ።” የሚሉት ነገር አላቸዉ።
“ምን ዋጋ አለዉ በስተመጨረሻ ጓያ ሰባብሮ ጣለዉ እንጂ።”
ይህ የጓያ ነገር ጥያቄ ስለሆነብኝ በማግስቱ ሲነጋ ጠብቄ ሳይንሳዊ መልስ ለማግኘት ሙከራ አደረኩኝ። እኔ የሳይንሰ ጋዜጠኝነት ስለምሰራ ሳይንሳዊ ምላሽ ማግኘት ግዴታዬ ነዉ። ይሁንና እናቴ የጓያ ክምር በፀሃይ ሲመታና የጓያዉ ፍሬ ሲቀቀል የሚወጣዉ እንፋሎት ጉልበትና እግር እንደሚሰብር የነገረችኝንም ሙሉ በሙሉ መቃወምም አለፈለኩም።
ምክንያቱም እናቶቻችንና አባቶቻችን ጋር ያለዉ ሀገራዊ እዉቀት ምንም እንኳን በትክክል በሳይንሳዊ መንገድ ተጣርቶ ጥንቅቅ ብሎ ተመዝግቦ ባይያዝም ተመንዝሮ የማያልቅ የእዉቀት መነሻ እንዳላቸዉ የ6 ኪሎ የስነፅሁፍ መምህሮቼ በሚገባ ነግረዉኛል።

ጓያ እና በዉስጡ ያለዉ መርዛማ ንጥረ ነገር
በመሆኑም ሀገራችን ኢትዮጽያ ካፈራቻቸዉ ምሁራኖቿና ዉድ ልጆቿ መሃል አንዱ ወደሆኑት ወደ ዶ/ር ካሳሁን ተስፋዬ (የኢትዮጽያ ባዮና ኢመርጅንግ ቴክኖሎጅ ኢንስቲቱዩት ዋና ዳይሬክተር) በተንቀሳቃሽ ስልኬ ሳይንሳዊ ምላሽ ለማግኘት ጥያቄዎቼን ላኩኝ ”ዶ/ር እንደምን ዋልክ። ስለ ጓያ ጥያቄ ላነሳልህ ነበር። “ጓያ የሰብራል” የሚባለዉ ነገር? ሳይንሳዊ ድጋፍ አለዉ? በዚህ ዙሪያስ የተጠና ጥናት ይኖረን ይሆን?“ የሚል ጥያቄ።
ዶ/ር ካሳሁንም ወዲያዉ በፍጥነት፦
“Yes. ጓያ ይሰብራል ::
ODAP የሚባል ንጥረ ነገር ውስጡ አለው እርሱ የእግር ነርቭን ይጐዳል።
በምርምር ግን አነስተኛ ODAP መጠን ያለው ጓያ በሌላ አለም አለ።” የሚል ምላሽ ላከልኝ።
ሳይንሳዊ ሀሳብ ባለማቅረብ የጠረጠርኳትን እናቴን ባካበተችዉ ልምድ በዉስጤ እያደነኳት እያለሁ ወዲያዉ በማስከተልም “Lathyrus sativus (grass pea) and its neurotoxin ODAP” በሚል ርዕስ በአሜሪካዉ ናሽናል ላይብራሪ ኦፍ ሜዲስን የታተመ ጥናታዊ ጽሁፍ ላከልኝ። እኔም ለሰጠኝ ፈጣን ምላሽ አመስግኘዉ ጽሁፍን ማንበበ ቀጠልኩ።
ጓያ ከፍተኛ የካርቦሃይድሬትና የፕሮቲን ምንጭ ነው፡፡ ከክብደቱ 58% የሚሆነው ካርቦ ሃይድሬት፣25% ደግሞ ፕሮቲን ሲሆን ዝቅተኛ የቅባት ይዘትና ከፍተኛ የካልሺየምና የፎስፎረስ ማዕድናትን በውስጡ ይዟል፡፡
ይሁንና ከፅሁፉ እንደተረዳሁት በሳይንሳዊ ስሙ Latres Sativa (ላትረስ ሣቲቫ) የሚባለዉ ጓያ በፍሬ ዉስጥ ኒውሮቶክሲን (Neurotoxin ODAP) የተሰኘ ዋነኛ መርዛማ ንጥረ ነገር በብዛት ይገኛል።
ጓያና የጤና ጠንቁ
ሰዎች ጓያን በየእለቱ በብዛት በተከታታይ ሲመገቡና ከምግባቸዉ ከአንድ ሶስተኛዉ በላይ በሚሆን ጊዜ በእግሮች ላይ ብሎም በወገብ ኣካባቢ ጉዳት በማድረስ ለሽባነት ይዳርጋል። አንድ ጊዜ በጓያ የተጎዳ ሰዉ በህክምና ስለማይድን ችግሩ የዕድሜ ልክ የአካል ጉዳት ያደርስበታል።ለህመሙ የሚጋለጡት ደግሞ በአብዛኛው ወንዶች ናቸው፡፡
በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት መረጃ መሰረት ጓያን በስፋት እያመረቱ ለምግብነት የሚጠቀሙ ሰዎች በተለይም ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 45 የሚደርሱ ወንዶች፣ ከወገብ በታች ያለውን የሰውነት ክፍሎቻቸውን በመሰባበር ለአስከፊ ጉዳት የሚዳርጋቸው ሲሆን ችግሩ በህክምና ሊፈወስ የማይችል በመሆኑ ተጠቂው የዕድሜ ልክ ሽባ ይሆናል፡፡
“ጓያን በተደጋጋሚ መመገብ መርዛማነቱ በተለያየ መጠን ወደ ሰውነታችን እንዲገባ መፍቀድ ሲሆን በጓያ ውስጥ የሚገኘው ቤታ አዶኝ የተባለው ንጥረ ነገር በአንጐላችንና በህብለ ሰረሰራችን ውስጥ በመከማቸትና የነርቭ ስርዓታችንን በማዛባት፣ ከወገብ በታች ስብራትን ያስከትላል ተብሏል፡፡”
” ጉዳቱ እንደ ሰውየው የጤንነትና የአቅም ሁኔታ የሚለያይ ሲሆን ከቅጽበት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ የጊዜ ገደብ ውስጥ በጓያ ሳቢያ ለሚከተለው የጤና ችግር ተጠቂ ይሆናል፡፡ በጓያ ምክንያት የሚመጣው ስብራት፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ የቻይና፣ የህንድና የባንግላዲሽ ህዝቦችን ለዓመታት ሲያጠቃ መቆየቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡”
በአገራችን ጓያ በስፋት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች መካከል ጐጃም፣ ጐንደር፣ ሸዋ፣ ወሎና ትግራይ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ አነስተኛ እርጥበት ወይም ከፍተኛ የውሃ ክምችት ባለበት ሥፍራ መብቀል የሚችል ሲሆን በእርሻ ላይ የናይትሮጂን መጠን በመጨመር፣ የአፈርን ለምነት የማሻሻል ብቃት አለው፡፡
የጅማት መሸማቀቁ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና ስር እየሰደደ ሄዶ ተጠቂው በድንገት መንቀሳቀስ ያቅተዋል፡፡
እንደ ህክምና ባለሞያዎች ከሆነ የጓያ ስብራት ህመም ምልክቶች ቅጽበታዊ የሆነ የጡንቻ መሸማቀቅ ስሜት በእግር ላይና ባት አካባቢ መሰማት፣ እግር ባት አካባቢ የሚታይ አነስተኛ እብጠት፣ በጭንና በታፋ ላይ የህመም ስሜት፣ የእግር አውራ ጣትና መዳፍ አካባቢ በቀላሉ አልታዘዝም ማለት፣ የእግር ጡንቻዎች ላይ የህመም ስሜት ናቸዉ።
በጓያ ስብራት የተጠቃ ሰዉ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስም በእጅጉ ይቸገራል፡፡ የጓያ ስብራት ከሚያሳድረው የጤንነት ችግር በተጨማሪ ስነልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖው እጅግ አስከፊ እንደሆነ የጠቆመው ጥናቱ፤በሽታው ከመከሰቱ በፊት በተለያዩ መንገዶች መከላከል እንደሚቻል ገልጿል፡፡
ዋንኛ የጓያ ስብራት መከላከያ መንገድ ጓያን ለምግብነት ከማዋል በፊት በውስጡ የያዘውን አደገኛ መርዛማ ንጥረ ነገር በተለያዩ ዘዴዎች ማስወገድ ነው፡፡ ለምሳሌ በፈላ ውሃ መዘፍዘፍ አንዱ መንገድ ነው፡፡ ከሚዘፈዘፈው ጓያ በአራት እጅ የሚበልጥ ውሃ አፍልቶ ለሰዓታት መዘፍዘፍና ደጋግሞ በቀዝቃዛ ውሃ እያጠቡ መርዛማ ንጥረ ነገሩ አስወግዶ በፀሐይ ማድረቅ፣ አሊያም ጓያውን በቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ ለ12 ሰዓታት ያህል በመዘፍዘፍ ውሃውን ማስወገድ፣ በመቀጠልም እርጥቡን የጓያ ፍሬ በእንፋሎት ከ20 እስከ 30 ደቂቃ ማፈን፣ በመቀጠልም በቀዝቃዛ ውሃ ለአንድ ሰዓት ያህል መዘፍዘፍ፤ ከዚያም ውሃውን ማጥለልና በፀሐይ ማድረቅ፡፡ ሁለቱ ዘዴዎች በጓያው ውስጥ የሚገኘውንና ከ80-90% የሚሆነውን መርዛማ ንጥረ ነገር ለማስወገድ እንደሚያስችሉ ታውቋል፡፡
በምርምር የተሻሻለና መርዛማነቱ የተወገደ ጓያ የማዉጣት አስፈላጊነት
ዶ/ር ካሳሁን እንደጠቆሙት በሌላዉ አለመ በምርምር የተሻሻለና መርዛማነቱ የተወገደ ጓያ በጥቅም ላይ እየዋለ በመሆኑ በጤና ላይ የሚያስከትለዉ ጉዳትን መከነስ ተችሏል። በሀገራችንም በተመሳሳይ በተለይም በዘረመል ዓርትኦት በበርካታ የሰብል አይነቶች ለምሳሌ በጎመን ዘር ዉስጥ ያለዉን ተመሳሳይ ጎጂ ንጥረ ነገር ለማረም ፣ የጤፍን መጋሸብና መዉደቅ ለማስቀረት እንዲሁም በማሽላ አቀንጭራ ላይ እየተደረጉ እንዳሉ ምርምሮች በጓያ ዝርያችን ላይም ተመራማሪዎቻችን ስራ መስራት ይኖርባቸዋል።
ወይም አስቀድመዉ በሌሎች አገራት የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማምጣት ማላመድና ላችግሩ ዘላቂ መፍተሄ መስጠት ይገባል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ቻይና፣ ህንድና ባንግላዲሽ ለጓያ ስብራት ችግር ተጋላጭ መሆናቸው ይነገራል። ጓያ በብዛት ጐርፍና የድርቅ አደጋን ተቋቁሞ ከባህር ወለል በላይ ከ1800-2000 ሜትር በዋልካ አፈር ላይ የመብቀልም ብቃት አለዉ፡፡ የጓያ ሰብል ከ150 በላይ ዝርያዎችም አሉት፡፡
