
ትግራይ
የተባበሩት መንግስታት የምግብ ፕሮገራም ኤጀንሲ (WFP) በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ለተራቡ ሰዎች መከፋፈል የሚገባዉ የእርዳታ ምግብ የተዘረፈ በመሆኑ በዝርፊያዉ ዙሪያ የውስጥ ምርመራ በመጀመሩ ርዳታውን አቁሟል ሲል AP ኒዉስ ዘግቧል።
የተባበሩት መንግስታት የአለም የምግብ ፕሮግራም እና ከሌሎች አጋሮች እህል ወደ ትግራይ የማድረስ ሀላፊነት አለባቸዉ፣ ለሁለት አመታት የዘለቀውን አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት በህዳር ወር በተደረሰዉ ስምምነት መሰረት መቆሙ ይታወቃል።
በክልሉ ከሚኖሩት 6 ሚሊዮን ሰዎች መካከል በአሁኑ ጊዜ ከ5 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ህይወታቸዉ በእርዳታ ላይ የተመሰረተ ነው ሲል አራት የተባበሩት መንግስታት የግብረሰናይ ሰራተኞችን ጠቅሶ ዘገባዉ ጠቁሟል።
እንደ ዘገባዉ ከሆነ የምግብ ክፍፍል ፍትሃዊነት በተዘገበበት ወቅት WFP ለሰብአዊ አጋሮቹ ባለፈው ሚያዝያ 20 ቀን የምግብ እርዳታ ለግዜው ማቆሙን አስታውቆ እንደነበር ከአራቱ ግብረሰናይ ሰራተኞች መካከል አንዱ ለኤፒ ተናግሯል።
ሌሎች ሶስት የእርዳታ ሰራተኞችም መረጃውን አረጋግጠዋል። የዜና ምንጮቹ በመስሪያ ቤታቸው ደንብ መሰረት በዚህ ጉዳይ ላይ በቀጥታ ጋዜጠኛ ለማናገር ስልጣን ስለሌላቸው ሁሉም ስማቸው እንዳይገለጽ አጥብቀው ጠይቀዋል ሲል ኤፒ ኒዉስ ዘግቧል።።
በWFP የኢትዮጵያ ዳይሬክተር እ.አ.አ በኤፕሪል 5 ቀን በላከው ደብዳቤ የሰብአዊ ሥራ አጋሮቹን “የምታውቁትን ወይም በሰራተኞቻችሁ ፣ በተጠቃሚዎችዎ ወይም በአከባቢዎ ባለስልጣናት ዙሪያ በሚቀርበውቀ እርዳታ ዙሪያ ማንኛውንም መረጃ ወይም የምግብ አጠቃቀም ችግር ካለ፣ አላግባብ የመጠቀም ወይም አሰራሩን የማስቀየር ጉዳይዮች ከታዩ መረጃውን እንዲያካፍሉ።” ብሎ መጠየቁን አስታውሰዋል።
በወቅቱ ሁለት የእርዳታ ሰራተኞች ለኤፒ እንደተናገሩት የተሰረቁት እቃዎች 100,000 ሰዎችን ለመመገብ የሚያስችል በቂ ምግብ ያካተተ ነበር። ምግቡ በትግራይ ሸራሮ ከሚገኝ መጋዘን ውስጥ ነው የጠፋው። ይሁንና ለስርቆቱ ተጠያቂው ማን እንደሆነ አልታወቀም።
የትግራይ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ባለፈው ወር የኤጀንሲው ሀላፊዎች በክልሉ ርዕሰ መዲና መቐለ ባደረጉት ጉብኝት ከ WFP ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር “ እየተባባሰ በመጣው የእርዳታ አቅርቦትና ሽያጭ ፈታኝ ሁኔታ ዙሪያ” መወያየታቸው ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የ WFP ቃል አቀባይ አስተያየት እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄም ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጡም ብሏል ዘገባዉ።
