
በመኮንን ተሾመ ቶሌራ
ባለፉት አራት አመታት በምስራቅ አፍሪካ አጋጥሞ በማያውቅ ሁኔታ የበረሃ አንበጣ የመንጋ ወረራ አጋጥሟል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና ትግበራ ማዕከል (ICPAC) ከኢጋድ አባል አገራትና ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን በአንበጣ መንጋን ዙሪያ ትንበያ፣ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና የጊዜ ጥቆማን ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል።
በሀገራቱ መካከልና ኢጋድ እንዲሁም በሌሎችተባባሪ አካላት ያለዉ ትብብር የሚደያ ባለሞያዎችን በማካተት “ድንበር ለማያዉቀዉ የበረሃ አንበጣ ፣ድንበር ዘለል መፍትሔ።” ለመስጠት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የማዕከሉ ባለሞያዎች አስታዉቀዋል።
የኢጋድ አንበጣ ቁጥጥር ሥራ
የማዕከሉ ባለሞያዎች እንዳሉት ከሆነ የበረሃ አንበጣዎችን፣ ሰብል አዉዳሚ ወፎችን እና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ተባዮችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መቆጣጠር ሰብሎችን ለመከላከልና በኢጋድ ክልል የምግብ ዋስትናን ለማሻሻል ወሳኝ ነዉ ።
ባለሙያዎቹ ይህንን የገለፁት ከንዑስ አህጉሩ ለተዉጣጡ ጋዜጠኞች ማዕከሉ “የበረሃ አንበጣ እና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ተባዮች ወረራ በኢጋድ ቀጠና” በሚል መሪ ቃል በኬንያ ናይቫሻ ከተማ ስልጠና ባዘጋጀበት ወቅት ነዉ።
በወቅቱ የ ICPAC-IGAD የምድር ምልከታ እና የጂኦ-መረጃ ባለሙያ እና በምግብ ስርዓት እና የምግብ ዋስትና ላይ የፖሊሲ ልማት ባለሙያ የሆኑት ሚስተር ኬኔት ምዋንጊ እንዳስታወቁት በኢጋድ ቀጠና በበረሃ አንበጣ እና በሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ተባዮች ምክንያት ከፍተኛ የሰብል ውድመት ስለሚከሰት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ድሃ ገበሬዎች የምግብ ዋስትና ችግር ሲያጥማቸዉ ይስተዋላል።
“ስለሆነም የኢጋድ አባል ሀገራት ተደጋጋሚ የበረሃ አንበጣዎችን፣ ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ተባዮችን እና በመንጋ የሚጓዙ ሰብል አዉዳሚ ወፎችን በብቃት መቆጣጠር ከቻሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮቻችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ይቻላል።”
አንበጣና ከፍተኛ የሰብል ውድመት
እንደ ኬኔት ገለጻ፣ እ.አ. አ በ2023 ብቻ 5.5 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት 60 ቶን እህል በምዕራብ ኬንያ በወፎች ወድሟል። በተጨማሪም የኡጋንዳ የግብርና፣ የእንስሳት ኢንዱስትሪ እና አሳ ሀብት ሚኒስቴር እንደገለፀዉ በጎርጎሮሳዊው ዘመን አቆጣጠር 2020ዓ.ም. 5.5 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት 7000 ሜትሪክ ቶን ሩዝ ወድሟል።
ይህ በገበሬዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል እና ለምግብ ዋስትና ችግር የሚዳርግ ከፍተኛ መጠን ያለው የሰብል መጠን ነው። ከዋና ዋናዎቹ በወፎቹ የሚጠቁት የሰብል አይነቶችም ሩዝ፣ ማሽላ፣ ስንዴ፣ ማሽላ፣ ጤፍ እና ገብስ እንደሚገኙበት ኬኔት ጠቁመዋል።
እንደ ባለሙያው ከፍ ያለ የሙቀት መጠን የተባዮቹን የእንቁላል የመፈልፈያ እና የአንበጣ መራባትን የሚጨምር ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥም በተለያዩ ተባዮች የሚደርሰውን የሰብል ወረራ ከሚያባብሱ ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ነዉ።
የICPAC-IGAD የመረጃ አያያዝ ባለሙያ ሚስተር ኸርበርት ሚሲያኒ በበኩላቸው እንደ ኤልኒኖ ያሉ የአደጋ መንስኤዎች መስተጋብር፣ ወቅታዊ ድርቅ እና ጎርፍ በኢጋድ አካባቢ ያለውን ተጋላጭነት እያባባሱ እና የቀጠናውን የሙቀት መጠን በመጨመር ተለዋዋጭነት እንደሚያባብሱ ጠቁመዋል። ቀጠናዉ እየሞቀ በሄደ ቁጥር አንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ርጥበት ሊያገኙ ሲችሉ ሌሎች ደግሞ የዝናብ እጥረት ሊያጋጥማቸው ይችላል ሲሉም አክለዋል። ይህም ለአንበጣ መራባት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።
የ ICPAC-IGAD የኮሙዩኒኬሽንና ኦፊሰር ወይዘሮ እመቤት ጂግሳ በተጨማሪም የአየር ንብረት መዛባትን የሚያስከትሉ አደጋዎችን ለመቆጣጠር እና ለመተንበይ እና የማህበረሰብን የመቋቋም አቅምን ከማሻሻል ጋር በተገናኘ ከ ICPAC አገልግሎቶች መካከል አንዱ እንደመሆኑ መጠን የማህበረሰብን የመቋቋም አቅምን ከማጎልበት ጋር ተያይዞ ICPAC ጠንከር ያለ የመገናኛ መሳሪያዎችን አዘጋጅቷል ብለዋል።
በኢጋድ ክልል ያሉ የተቋማት አቅም መገንባትና ለአባል ሀገራቱም ተዛማጅ መረጃዎችን በማሰራጨት እና በማካፈል ተጋላጭነትን ለመቀነስ ማዕከሉ እየሰራ ነዉ ብለዋል።
ከICPAC አገልግሎቶች መካከልም የአየር ንብረት ትንበያ፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ የዳሰሳ ጥናት፣ የአካባቢ ክትትል እና የመረጃ ስርጭት ሲሆኑ እነዚህም ለምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ ልማት በሚሆን መልኩ እንደሚተገበሩ ተናግረዋል።
እንደ ወይዘሮ እመቤት ገለጻ፣ ICPAC በክልሉ ያለውን የአደጋ ክትትልና ትንበያ አቅም ለማሳደግ እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን እና ማህበረሰቡን ሳይንሳዊ መረጃ የመቀበልና የመጠቀም ሁሌታ ለመጨመር እንዲሁም የአየር ንብረት አገልግሎትን ውጤታማ በሆነ የግንኙነት እና የመረጃ ልውውጥ አቅም ለማሳደግ ይሰራል።
በተጨማሪም ICPAC የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ፣ የአየር ንብረት አገልግሎቶችን ተደራሽነት እና አጠቃቀምን ለማረጋገጥ ፣ የምድር ምልከታ እና የጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂዎችን ለአካባቢ እና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ በቀጠናዉ ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲሁም አቅሞችን ለማጠናከር እንደሚሰራ ተጠቁሟል። አባል ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳን እና መላመድን ለመፍታትም ማዕከሉ አልሞ እየሰራ ይገኛል።
ኢጋድ የበረሃ አንበጣን እና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ተባዮችን በዘላቂነት ለመቆጣጠር የሚያስችል ንዑስ-ክልላዊ መድረክን አቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል። መድረኩ የኢጋድ አባል ሀገራት ለሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ምላሽ እንዲሰጡ የሚደግፍ ነው። የበረሃ አንበጣ ወረራ እና የተባዮች መከላከል ስልቶችንም ይነድፋል።
ICPAC፣ አሁን ላይ በምስራቅ አፍሪካ የክልል የአየር ንብረት ማዕከል (WMO-RCC) በኩል የዓለም የሜትሮሎጂ ድርጅትን (WMO) ወኪል ሲሆን፣ የAUC/NEPAD የውሃ ማእከላት የልህቀት ማእከል አባል ሲሆን በ UNFCCC የታዛቢነት ወንበርም አለዉ።
በቢሊዮን የሚቆጠሩ አንበጣዎች በአንድ ጊዜ በአንድ አካባቢ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ ሲሆን የሚሸፍኑትም ቦታ በመቶዎች ኪሎ ሜትር ሊሆን ይችላል። የአንበጣ መንጋው በቀን እስከ 200 ኪ.ሜ በመሸፈን ያገኙትን እየበሉ በመራባት የአርሶ አደሮችን ህይወት አደጋ ላይ ይጥላሉ። አማካይ የአንበጣ መንጋ 2500 ሰዎችን ለዓመት የሚመግብ ምርትን ሊያወድም ይችላል። አንድ አንበጣም ከራሱ ክብደት በላይ የሆነ ሰብል ሊበላ ይችላል።
