

በግርማ መንግሥቴ
ቅይጥ ዘረ-መል ብዝኃ ሕይወትንም ሆነ ባዮቴክኖሎጂን፤ እንዲሁም ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በተመለከተ ኢትዮጵያ አዲስ አይደለችም። በተለይ “BIOSAFETY REGULATORY LEGAL FRAMEWORKS OF ETHIOPIA″ (A∙A 2022) በሚል ስያሜ በአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አማካኝነት፣ ባለቤትነት በርካታ ጉዳዩን የተመለከቱ መንግሥታዊ መመሪያዎች ይፋ የተደረጉበትን ሰነድ፤ እንዲሁም በርካታ ባህላዊና ጥንታዊ የግብርና አሰራራችንን፤ አመራረትና አሰባሰባችንን በቅርብ ለሚያውቅ ሰው አገራችን ለጉዳዩ አዲስ አለመሆኗን (ዝቅ ብለን የምናየው ሆኖ) በሚገባ ይገነዘባል።
ስብስብ መመሪያና ደንቦችን ከያዘው ከዚህ ጥራዝ መረዳት የሚቻለው የላይኛውን ብቻም አይደለም፤ ኢትዮጵያ ምን ያህል ከበርካታ አፍሪካ አገራት ቀድማ ጉዳዩ የሕግ ማእቀፍ ይኖረው ዘንደ የሰራች ቀዳሚት አገር መሆኗንም መገንዘብ ይቻላልና ጥራዙን መመልከቱ ተገቢ ይሆናል።
(እዚህ ጋ፣ ከባዮቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ ሰፋ ባለ መልኩ ለመገንዘብ በጄኔቲክ የተሻሻሉ አካላት፣ ስጋት፣ የአደጋ ግምገማ፣ የጄኔቲክ ምህንድስና፣ የጄኔቲክ አርትኦት፣ የህይወት ጥራት፣ ብዝሃ ህይወት፣ ኢኮኖሚክስ፣ አካባቢ፣ ዲኤንኤ፣ የጥንቃቄ መርህ፣ ትራንስጀኔቲክስ፣ ባዮሴፍቲ እና ሌሎችንም በቁልፍ ቃላትነት ለይቶ መመመርመር ጠቃሚ መሆኑን በቅንፍ አስቀምጦ ማለፉ ተገቢ ይሆናል።)
ባዮቴክ እንደ አገር አሜሪካንን አስቀድሞ በርካቶችን ምርታማና ሲበዛም አትራፊ ከማድረግም አልፎ ለሌላው እስኪተርፉ ድረስ እያንበሸበሻቸው የሚገኝ ሲሆን፤ እንደ ግለሰብም ካየነው ህንዳዊውን ዲሊፕ (Dilip Shanghvi) ባለ US$25.7 ቢሊዮን ቱጃር በማድረግ የሀብት ሰገነት ላይ አስቀምጧል። ሌሎችንም እንደዛው። ይህ የሚያስተምረው አቢይ ጉዳይ ቢኖር በአገራችን ኢንቨስት የሚደረገው በህንፃ ላይ ብቻ ሳይሆን አገርንና ሕዝብን በሚጠቅመው ባዮቴክኖሎጂ ላይም መሆኑን ነውና ከዚህ በኋላ (ሌሎች መጥተው እድሉን ሳይወስዱት) የአገራችን ባለሀብቶች ያስቡበታል ብለን እናስባለን።
በዘርፉ ባለሙያዎች “የስነህይወት ፍጥረታትን እንደ የእንስሳት ህዋሳት፣ የእፅዋት ህዋሳት፣ የደቂቅ ኣካላት ህዋሳትን እንዲሁም የእነሱ ተዋፅኦ የሆኑ እንደ ኢንዛይም ያሉ ክፋዮችን በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በህክምና፣ በመድሃኒት ምርት ሂደት ውስጥ መጠቀም ማለት ነው።″ በሚለው ትርጓሜው መግባባት ላይ የተደረሰበት ባዮቴክኖሎጂ ወደ ግብርናውና ሌሎች ዘርፎች በማምጣትና ጥቅም ላይ በማዋል አገራት ተጠቃሚ እየሆኑ ሲሆን፤ በተለይም (እንደየቅደም ተከተላቸው (አሜሪካ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያ፣ እና ዴንማርክን) የሚደርስባቸው የለም።
በባዮቴክኖሎጂ መሳሪያዎች አምራችና ተጠቃሚነት አኳያም ሰሜን አሜሪካ (በ2023) 37·79% ዶላርን ከዘርፉ በማፈስ ፊት መሪነቱን እንደያዘች ነች። 23·99% በማግኘት እሲያ ፓሲፊክ 2ኛ፤ ከዘርፍ አኳያ ስንመለከተው ደግሞ ህክምናው (ባዮፋርማሲ) 41·73%፤ ኢንዱስትሪው (ባዮኢንዱስትሪ) 24·33% በመሆን የ1ኛ እና 2ኛነት ደረጃን ይዘው እናገኛቸዋለን።
የባዮቴክኖሎጂ ምርቶች በአለም ገበያ ላይ በከፍተኛ ደረጃ እየመሩ ሲሆን፣ በ2023 $1·38 ትሪሊዮን የደረሰው፤ በ2030 $3.88 ትሪሊየን፣ በ2033 4·25 ትሪሊዮን ይደርሳል ተብሎ ተተንብዮለታል። ይህም ከ2024 ጀምሮ እስከ 2033 ድረስ በየአመቱ አጠቃላይ አመታዊ የገበያ እድገቱ (CAGR) 11·8% መሆኑን ያመለክታል።
ከዚህ መረጃ መረዳት የሚቻለው ዘርፉ እጅጉን አዋጭና ባለ ሀብቶችን እሚያበረታታ መሆኑን ነውና በአገራችንም ሊታሰብበት ይገባል እንላለን።
“አጠቃላይ ካፒታል አኳያ መረጃው ሊገኝ አልቻለም″ (“The top-performing countries in biotechnology (according to the OECD)″ን ይመለከቷል) የተባለላትና በህክምናው (domestic pharmaceutical sector) ዘርፍ ብቻ ከ4ሺህ 441 በላይ የባዮቴክ ካምፓኒስ እንዳሏት የምትገመተውን ቻይና ትተን፤ በስራ ላይ ያሉ (active biotech companies) 2ሺህ 840 ኩባንያዎች ያሏትን፤ የአሜሪካንን የባዮቴክኖሎጂ ምርቶች ገበያን ስንመለከት በ$246·18 ቢሊዮን (በ2023) ዋጋን በማስመዝገብ (ከባለፈው አመት 11·90% እድገት ማለት ነው) በ1ኛነት ደረጃ አለምን እየመራ የሚገኝ ሲሆን፤ ይህም በ2033 $763·82 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ተገምቷል) ይገኛል። በዚሁ አመት ሰሜን አሜሪካ ከአለም የ41% ድርሻን እንደያዘችም ተነግሯል።
ይህ የአገራቱ መልካም ተሞክሮ ወደ አፍሪካ የማይመጣበት ምንም ምክንያት የለምና እንደ አህጉር አፍሪካ፤ እንደ አገርም ኢትዮጵያ አሁን ብልጭ ብልጭ (አንዳንዴም ብልጭ ድርግም) እያለ ያለውን የባዮቴክኖሎጂ ዘርፍ በዚሁ ቅኝት ውስጥ መመልከት ጠቃሚ ይሆናል።
ለ94ሺህ 579 ሰዎች የስራ እድል በፈጠረው፣ በዩኬ በ2023 የባዮቴክ ገበያ (market size) £21.8 ቢሊየን የነበረ፤ አገሪቷም 2ሺህ 800 በስራ ላይ ያሉ ኩባንያዎች ያሏት (ከአሜሪካ ቀጥሎ ማለት ነው) መሆኑን ይዘን (ዝርዝሩን ከBiotechnology in the UK – Market Size, Industry Analysis, Trends and Forecasts (2024-2029) ማየት ይቻላል)፤ ወደ ቦስተንና አካባቢው ያለውን የባዮቴክኖሎጂ ልማትና አስመጭ፣ ላኪ እና አትራፊ ኩባንያዎችን የተመለከተ ዝርዝር ከLabiotech.eu. ድረ-ገጽ መመልከት ይቻላል።
ወደ አፍሪካ ስንመጣ፣ በተለይ በ2008 በግብርናው (ጥጥ፣ በቆሎና በመሳሰሉ ሰብሎች) ዘርፍ ከፍተኛ ተጠቃሚ ሆነው የነበሩትን ቡርኪና ፋሶ፣ ግብፅና አንዳንዶችን፤ እንዲሁም በ2019 በጥጥ ምርት ከፍ ብለው ይታዩ የነበሩትን፣ ማላዊና ኢትዮጵያን ካልጠቀስን በስተቀር፣ ይህ የሌላው ዓለም ትርፋማነትና ተጠቃሚነት ህልም ሆኖ እናገኘዋለን።
በሌሎች፣ እንደ ኤዥያ፣ ላቲን አሜሪካና የመሳሰሉት የአደጉ አገራት የተትረፈረፉት ዘመናዊ የግብርና ግብአት ምርቶች፣ በአፍሪካ ጭራሽ ጥቅም ላይ አልዋለም ለማለት ሳይሆን፣ ውሏል ለማለት በሚያስቸግር ደረጃ አንዳንድ አገራት እየሰሩ ይገኛሉ። ለምሳሌ ግብፅ የመድሀኒት ምርቶችን በማምረቱ ሂደት በከፍተኛ ደረጃና ትኩረቱን በbio-pharmaceuticals ያደረገ የባዮቴክ የምርምር ስራዎችን በመስራት አህጉሪቱን እየመራች ሲሆን፤ ሴኔጋል በCrop Biotech ተጠቀሚነት ምርታማ በመሆን በ2ኛ፤ biotech cropsን ወደ ራሷ በማምጣትና ጥቅም ላይ በማዋል ከአህጉሪቱ አንደኛ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ በHealth Biotech አማካኝነት የጤና ዘርፉን በማልማት በ3ኛ ደረጃ፤ ኬኒያ የእንስሳት ጤናን በመጠበቅና ከእንስሳት ተዋፅኦ ተጠቃሚ መሆን ባስቻላት፣ በAnimal Biotech ላይ ምርምር በማድረግና ወደ ተግባር በማውረድ 4ኛ ደረጃን በመያዝ ከአፍሪካ ጎላ ብለው መታየት የቻሉ አገራት ናቸው። ለዝርዝሩ Status of Biotechnology in Africa: Challenges and Opportunities ማየት ይቻላል።
ጥናቶች (ለምሳሌ “Biotechnology Development in Africa″ (2023)) እንደሚያሳዩት በአፍሪካ 41 ሚሊዮን ባለትናንሽ መሬት ይዞታ ባለቤት ገበሬዎች ናቸው የአህጉሪቱን ሕዝብ የሚመግቡት። በመሆኑም፣ እንደ አህጉርም ሆነ እንደ አህጉሪቱ አገራት ከረሀብና ችግር ማምለጥ አልተቻላም። እነዚህ አርሶ አደሮች ደግሞ በበቂ ሁኔታ አምርተው አህጉሪቱን ከከፋ ረሀብ እንዳይታደጉ በተለያዩ ችግርች፤ ለምሳሌ ዝቅተኛ ምርት፣ የገበያ ውስንነት፣ በድህረ-ምርት መሰብሰብ ወቅት የሚደርስ ክስረት (post-harvest losses)፤ ዝቅተኛ የአፈር ጥራት፣ የውሀ እጥረት፣ መዋእለ-ነዋይን በተገቢው ያለማፍሰስ ችግር መኖር (chronic underinvestment)፤ የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት እና በሌሎችም ተጠፍንገው የተያዙ ሲሆን፤ በአህጉሪቱ ባዮቴክኖሎጂን በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ማዋል አለመቻላቸው ደግሞ ከሁሉም የከፋው የአህጉሪቱ ፖሊሲ አውጪዎች ችግር ሆኖ ይስተዋላል።
በግቡ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ድህነትን ማስወገድ በሆነውና ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ግብአቶችን (innovations) በሚፈልገው የአፍሪካ ግብርና የባዮቴክኖሎጂ አጠቃቀምም ሆነ ያለው አጠቃላይ ግንዛቤ በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑ አኳያ ችግሩን እንዲህ በቀላሉ የሚፈታ አይመስልም።
ከዚሁ ከአጠቃላይ ግንዛቤ ችግር ጋር በተያያዘ የተነሱ የባለሙያዎች አስተያየቶች ያሉ ሲሆን፣ አንዱም በታደሰ በዳዳ (ፒኤች·ዲ) የተሰጠው አስተያየት ነው።
ዶ/ር ታደሰ በዳዳ ባለፈው አመት ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ (ረቡዕ፣ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም እትም) ጋር ቆይታ አድርገው በነበረበት ወቅት እንደተናገሩትም ሆነ በደቡብ አፍሪካ (ፕሪቶሪያ) ከ8 – 12/2024 (ኤፕሪል) በተካሄደ፣ “Crisis Communication″ን አስመልክቶ ሰፊ ውይይት በተካሄደበትና የባዮሴፍቲ ቁጥጥርን የተመለከተ ጉባኤ ላይ እንደ ተገለፀው የቴክኖሎጂው ተቃዋሚዎች (ኦፖነንትስ) የሚነዙት ጥቅማቸውን ብቻ ማእከል ያደረገ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ (የሀሰት ትርክት) ዋናው ሲሆን፤ የቆየና ሳይንሳዊ መሰረትን ያልያዘው አስተሳሰብ (ሚት)ም የራሱን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ሌላው የአፍሪካ ግብርና መሰረታዊ ችግር መንግስታት (ከ54ቱ 48ቱ) ለግብርናው ዘርፍ ዝቅተኛ በጀት (3.8 ከመቶ) መመደባቸው ሲሆን፤ ይህ በመስኩ የሚሰማራ ባለ ሀብት ካለ መኖሩ (እጥረት መኖሩ) ጋር ተዳምሮ ዘርፉን የቀጨጨ ማድረጉ በዚሁ ከላይ በጠቀስነው ጥናት ውስጥ ተጠቅሶ ይገኛል። እንደ ጥናቱ ከሆነ ከድህነት መውጣትን ፈልጎ፣ ለዘርፉ በጀት ነፍጎ የሚሆን ነገር አይደለምና የአፍሪካ መንግሥታት አሰራራቸውን ሊመረምሩ፤ ባዮቴክኖሎጂን (ባለሙያዎቹ biotech crop adoption ይሉታል) መጠቀም ይገባል።
ይህ ከ54ቱ 48ቱ በአማካይ 3.8 ከመቶ በጀትን ይመድባሉ ይባል እንጂ ከበጀታቸው 1 ከመቶ ብቻ የሚመድቡ የአፍሪካ አገራት እንዳሉ በጥናቱ መጠቀሱን እዚህም ጋ መግለፅ ያስፈልጋል።
አፍሪካ ከ2019 ወዲህ፣ ካላት 190 ሚሊዮን አምራች ሄክታር መሬት ውስጥ 3 ሚሊዮን ሄክታሩን ብቻ ድርቅን ለመቋቋም፣ በሽታን ለመከላከል፣ አረምን ለመቆጣጠር፣ ቫይረስን ለመቋቋም ወዘተ የሚያስችሉ የባዮቴክኖሎጂ ምርቶችን የተጠቀመች አህጉር ነች። በመሆኑም ይላል ይሄው የቅርብ ጊዜ ጥናት፣ አፍሪካ የባዮቴክኖሎጂ ልማት (Biotechnology development) እጅጉን ያስፈልጋታል።
የዘረመል ምንነት ከተገለጠበት ከ1960ዎቹ ጀምሮ በተለይም በ1970ዎቹና በ1980ዎቹ ውስጥ በፍጥነት እያደገ የመጣው፤ ከሥነ ሕይወት አካላትና ሂደት ጋር የተያያዘና ከዚያ የሚገኝን ዕውቀት፣ ዘዴ ወይም ውጤት ለጤና አገልግሎት የማዋል ትግበራ የሆነው፤ እንዲሁም፣ አዳዲስ መድኃኒቶች፤ ፈጣን የመመርመሪያ ዘዴዎች፤ ክትባቶችና የተሻሻሉ የሕክምና መሣሪያዎችን እያስገኘ ያለው፤ አዳዲስ የዕውቀት አድማሶች እየተከፈቱ በመሄዳቸው የባዮቴክኖሎጂ ግስጋሴ እየጨመረ እንደሚሄድና የነገውን የጤና አገልግሎት ባህርይ እንደሚወስን የሚገመተው፤ የዘመኑ የሕክምና ደረጃ የሚጠይቃቸው የበሽታ መመርመሪያዎች፣ መድኃኒቶች፣ ክትባቶች፣ ማከሚያዎችና የመሳሰሉት የጤና ባዮቴክኖሎጂ ምርት ውጤቶች ለሕዝብ ጤና አገልግሎት መዳረስና ጥራት ሲባል የግድ አስፈላጊ መሆኑ የተመሰከረለት ዘመናዊ የጤና ባዮቴክኖሎጂ (medical-biotechnology) ወደ አፍሪካ አገራት ገብቷል በሚባልበት ደረጃ ላይ አይደለም (ይህንን በተመለከተ የተሟላ መረጃን ከወደ “የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲቲዩት″ ማግኘት ይቻላል)። በመሆኑን በአህጉሪቱ የጤና ችግር የጠና ከመሆን ገና አልተላቀቀም።
ሌላውና እዚህም እዛም በተደረጉ ጥናቶች ውስጥ በስፋት ተጠቅሶና ሰፋፊ ስፍራዎች ተሰጥተውት የሚታየው አፍሪካ ባዮቴክኖሎጂን ለማልማትና ስራ ላይ ለማዋል ከፍተኛ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የዘመናዊ ቴክኖሎጂና የባዮቴክኖሎጂ ፈተና፣ ትንተና፣ ሳይንሳዊ ምርምር እና ልማት፣ ፍተሻ እና ሌሎችንም ለማድረግ የሚያስችል የባዮቴክኒሎጂ ላቦራቶሪ እጥረት ያለባት የመሆኑ ጉዳይ ሲሆን፤ ይህም ያለ ማሰለስ ሊታሰብበት እንደሚገባ በእነዚሁ፣ እዚህ ባልጠቀስናቸአው በርካታ ጥናቶች ውስጥ ተገልፆ ይገኛል። ይህ ደግሞ ከግብርናውና ገበሬው፣ ከአህጉሪቱና ነዋሪዎቿም አልፎ ዳፋው ለአለም ኢኮኖሚ ሳይቀር የተረፈ በመሆኑ በዘርፉ የበለፀጉ አገራት ለአህጉሪቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል።
ሌላው፣ Masehela & Barros (2023)ን የሚጠቅሰውና የአፍሪካ ግብርና ላይ ብቻ ያተኮረው የAbdulkabir Abdulmalik ጥናት (Biotechnology Development in Africa) እንደሚያሳየው ከሆነ፣ ሌላው ከባዮቴክኖሎጂ ልማት ጋር በተያያዘ የአህጉረ አፍሪካ (በተለይም ከሰሃራ በታች) ችግር የ“ተደናግሬ″ (misconceptions) ወይም አረዳድ ችግር ሲሆን፤ ይህም አገራት ባዮቴክኖሎጂን የተመለከተና ራሱን የቻለ የፖሊሲ ማእቀፍ፣ ሕግና ደንብ እንዳይኖረው፣ እሚመራና እሚተዳደርበት መርህ እንዲያጣ አድርጎታል።
ይህ ሁሉ በሆነበት፣ በአሁኑ ሰአት አንድ ተስፋ ሰጪ ነገር ቢኖር ስምንት አገራት (ናይጄሪያ፣ ማላዊ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና፣ ኬኒያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ኤስዋቲኒ (Eswatini)) የተወሰኑ ምርቶችን በባዮቴክኖሎጂ በመታገዝ ለማምረት ፍላጎት እያሳዩ መምጣታቸው የሚበረታታ ሲሆን፣ ጋና በያዝነው የፈረንጆች አመት አራት ምርቶችን (cotton, soybean, maize, እና cowpea)፣ ሌሎች 10 አገራት ደግሞ በሙከራ ደረጃ የተለያዩ 33 የተዳቀሉ ሰብሎችን (genetically modified crops) ወደ መጠቀምና ማምረት በማምራት ላይ መሆናቸው፤ ይህም በ2018 $615.4 ሚሊዮን የነበረውን ዋጋ በ2025 በ5% ያድጋል ተብሎ መተንበዩና አጠቃላይ ዋጋውንም (value) $871 ሚሊዮን ያደርሰዋል ተብሎ መጠበቁ የአፍሪካ የባዮቴክ ተጠቃሚነት እየተሻሻለ በመሄድ ላይ ነው እሚለው ሚዛን እየደፋ በመምጣት ላይ ይገኛል።
ሌላውና አግሪ-ባዮቴክን በተመለከተ በአህጉሪቱ ትልቁ አክተር ኤኤቲኤፍ (AfricanAgricultural Technological Foundation) ሲሆን፣ እንደዚሁ መንግስታዊ ያልሆነና ለትርፍ ያልተቋቋመ አፍሪካዊና አፍሪካ ግብርና ተኮር ድርጅት ሪፖርት በአህጉሪቱ በቂ ነው ባይባልም የተወሰኑ መሻሻሎች አሉ።
የፋውንዴሽኑ የክንውንና አፈፃፀም ዘገባ እንደሚያሳየው፤
AATF በደረሰባቸው 23 የአህጉሪቱ አገራት 12ሚሊዮን 877ሺህ 887 አርሶአደሮችና ቤተሰቦቻቸውን ተደራሽ መሆን ተችሏል፤ 5ሚሊዮን 172ሺህ 122 በትናንሽ የእርሻ ቦታዎች ላይ አምራች አርሶ አደሮችን (Smallholder farmers) በመድረስ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። 81ሺህ 215 የገበያ ሰንሰለቶች ተፈጥረው ምርቶች ለገበያ እንዲቀርቡ ማድረግ ተችሏል። 451 ዘር አምራችና አዋዋዮች (Seed companies and agrodealers) እንዲሳተፉ ተደርጓል።
ይህ ብቻም አይደለም፣ እንደ የአፍሪካ ግብርና ቴክኖሎጂ ፋዉንዴሽን (AATF) 2022 ሪፖርት ከሆነ፣ 656,783 አርሶ-አደሮች በዘመናዊ የግብርና ልማትና ባዮቴክኖሎጂ አጠቃቀምን የተመለከተ ስልጠና አግኝተዋል፤ በእነዚሁ አገራትም 27ሺህ 694.87 ሜትሪክ ቶን አዳዲስ ምርቶች ተሸጠው በአጠቃላይ 1,176,394.8 ሄክታር መሬት በአዳዲስና ደህንነታቸው በተረረጋገጠ የግብርና ቴክኖሎጂ ምርቶች ለመሸፈን በቅተዋል። (ለበለጠ መረጃ የተቋሙን ድረ-ገጽ (https://www.aatf-africa.org/) አድራሻ ይመልከቱ።)
ወደ አገራችን እንመለስና ባዮቴክኖሎጂ ያለበትን አጠቃላይ ይዞታ እንመልከት።
በመግቢያችን ላይ እንደ ጠቀስነው፣ ባዮቴክኖሎጂን በሁለት ከፍለው (አሮጌውና ዘመናዊው) የሚያዩ (ያጠኑ) ሰዎች እንደሚሉት ባዮቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። እንደ እነዚሁ ሰዎች ድምዳሜ፤
“ሰዎች በዘልማድ ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ተግባራዊ እውቀት ሊጥ አቡክተው ዳቦ ወይም እንጀራ መጋገር፣ ብቅል፣ ጌሾና እንኩሮ ወይም ቂጣን ደባልቀው በመክደን ጠላን መጥመቅ፣ ማርን በማብላላት ጠጅ መስራት የወይን ፍሬን በመጭመቅና በማብላላት ወይን በቤት ውስጥ መስራት፣ ወተትን አልቦ በማስቀመጥ እርጎ እንዲሆን ማድረግ፣ እንሰትን ከትክቶ በማቡካትና በቅጠሉ ሸፍኖ መሬት ውስጥ በመቅበር ተብላልቶ ጣፋጭ ምግብ እንዲሆን ማድረግ፤ እነኚህንና መሰል ባህላዊ የተብላሉ ምግቦችን ማዘጋጀት (Traditional fermented foods) በውስጡ ባዮቴክኖሎጂ አለ። እዚህ ውስጥ ያለውን ባዮቴክኖሎጂ አሮጌው ባዮቴክኖሎጂ (Old biotechnology) እንለዋለን::″
ወደ አሁኑ፣ ዘመናዊው ዘመን እንምጣ።
በተጨባጭ እንደምንመለከው ከሆነ፣ በኢትዮጵያ የአካበባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ባለቤትነት በመግቢያችን የጠቀስነው ስብስብ ጥራዝ ውስጥ ያሉ መመሪያዎችና ሌሎችም በአግባቡ ስራ ላይ ይውሉ ዘንድ በመንግስት ተደንግጓል። በምን ያህል ሰዎችና የሚመለከታቸው አካላት እንደሚታወቅና ስራ ላይ እየዋለ እንዳለ አይታወቅም እንጂ ሰነዱ በመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች እጅ ሳይቀር ገብቷል። ገብቶም እንደየፕሮግራሞቹ አላማና ግብ ስራ ላይ እየዋለ ይገኛል ተብሎ ይታሰባል። ሆኖም፣ በቂ አለመሆኑ ደግሞ የዚያኑ ያህል ይነገራልና፤ በተለይ ኢትዮጵያ 192 ቢሊዮን ዶላር (ጂዲፒዋን) በማግኘት ወደ ላይ (ቶፕ ፋይቭ) ትመጣለች ብሎ አለም ቀመሩን ሰንዶ ለንባብ ባበቃበት ወቅት ያለ አግሪ-ባዮቴክ ሊሆን የሚችል አይደለምና ሰነዶቹን እንደ አንድ አስተማማኝ የህግ ማእቀፍ በመጠቀም ወደ ተግባር መግባት የሁሉም (ባለሀብቱን ጨምሮ) ሀላፊነት ሊሆን ይገባል።
መጋቢት 2014 (እአአ) ከAATF ጋር በትብብር መሥራት የጀመረው የግብርና ባዮቴክኖሎጂ መድረክ (OFAB-Open Forum on Agricultural biotechnology) ፕሮጀክቱ በሀገራችን የተጀመረ መሆኑን፤ ፕሮጀክቱ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ከማሻሻል፣ በዘርፉ ሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አከላትና ፖሊሲ አውጪዎችን በማገናኘትና ተቋማትን በማስተሳሰር ከግብርና ባዮቴክኖሎጂም ያለፈ ከፍተኛ ጠቃሜታ ያለው መሆኑን የሚያረጋግጠው፤ ድርቅንና ተባይን የሚቋቋም በቆሎ (TELA) በማምረትና ውጤት እያስመዘገቡና ፕሮጀክቱም ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ ጠቃሜታ ያስገኘና የአየር ለውጥን በመቋቋም ቴክኖሎጂን በመጠቀም የማህበረሰብን ብልጽግና ማረጋገጥ የሚለውን የAATF ግብ የሚመልስ መሆኑን “እነሆ በረከት″ የሚለው፤ የግብርና ተግዳሮቶችን ሊፈቱ የሚችሉ የባዮቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶችን በትብብር መስራቱንና በመደገፉ የአፍሪካ ቴክኖሎጂ ፋዉንዴሽንን (AATF) ከሚያወድሰው የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እንዲሁም፤
በAATF እና EIAR (የኢግምኢ) መካከል እየተከናወኑ የሚገኙ የትብብር ሥራዎችን የሚያደንቀውና በባዮቴክኖሎጂ ዙሪያም እየተሰራጩ ያሉ አግባብነት የሌላቸው ጉዳዮች መኖራቸውን በማወቅ ጉዳዩ ከተራ አሉባልታ ያልተለየና የግል ጥቅምን መሰረት ያደረገ መሆኑን የሚተቸው፤ በAATF እና የኢግምኢ የግብርና ቴክኖሎጂ ምርቶቸንና ሂደቶች ደህንነተ-ሕይወት ቁጥጥር (የአገሪቱን የባዮሴፍቲና ቁጥጥር መመሪያዎች ይመለከቷል) ላይም በትኩራት እየሰሩ እንደሆነ የሚያውቀው፤
በተጨማሪም∶-
ከቴክኖሎጂ ውጪ ያደገ አንድም አገር አለመኖሩን በመግለፅ የኢግምኢ ሁሌም ለሀገር ጠቃሚና ጉዳት የሌላቸውን የግብርና ቴክኖሎጂዎች በማፍለቅ፣ በመፈተሽና በማረጋገጥ ለማህበረሰብ ማቅረብ የሚገባው መሆኑ ላይ የሚያተኩረው፤ ለዚህም ሁሌም ከAATF ጋር አብሮ እንደሚሰራ ቃል የሚገባው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፤ እንዲሁም፣ እዚህ ያልጠቀስናቸው ሌሎች መሰል ተቋማት ሁሉ በዘርፉ ለሚሰማሩም ሆነ ለተመራማሪና አጥኚዎች ራሱን የቻለ የህግ ማእቀፍና የመረጃ ምንጭ ነውና ባዮቴክኖሎጂ ከአፍሪካዊው አጀንዳ 2023 በዘለለ ፋይዳው በርካታ በመሆኑ ማልማቱ ላይ የሁሉንም ርብርብን ይጠይቃል።
በአምስተ አመት ስትራቴጂ ማብሰር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከተገኙት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች መካከል አንዱ የሆኑትና የግብርና ትራንስፎርሜሽን (ATI) ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የOFAB 2022 ሻምፕዮን ዶ/ር ማንደፍሮ ንጉሴ AATF የተቋማትን አቅም በማሳደግ፣ ትጉ፣ ሥነ-ሥርዓትና ክሂሎት ባለው የሰው ኃይል እየገነባ መሆኑ ተገቢና በስትራቴጂው ውስጥ እተካተቱት ግቦች ላይ ለመድረስ መሠረታዊ መሆኑን መግለፃቸው፤ በአገራችን በOFAB ፕሮጀክት በኩል ስለ ባዮቴክኖሎጂ የአስተሳሰብ ለውጦች በፖሊሲ አውጪ፣ ተመራማሪዎችና ተጠቃሚዎች ዘንደ የተሻለ ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑን መናገራቸው፤ የባዮቴክኖሎጂ ውጤቶች ሌሎች የግብርና ሴክተሮች ጋርም እየደረሰ መሆኑን ማውሳታቸውና የመሳሰሉት ስለባዮቴክኖሎጂ ልማት የሚለው አንዳች ነገር አለና እዚህ መጥቀሳችን ፋይዳው ቀላል አይሆንም።
የባዮ እና ኢመርጀንግ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተርና በማላዊ የተካሄደው የOFAB አፍሪካ 2023 ዓ.ም ቻምፒዮን አሸናፊ ዶ/ር ካሳሁን ተስፋዬ ባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ከሶማሊ ክልል ሶስት ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነቱን በተፈራረሙበት ወቅት “በቀጣይም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት የክልሉን ማህበረሰብ የሚጠቅሙ ስራዎችን ለመስራት ኢኒስቲቲዩቱ ከክልሉ ጋር በጋራ እንደሚሰራ“ መናገራቸውም ሆነ፤ ኢትዮጵያ ከ1980 ዓ·ም ጀምሮ ባዮቴክኖሎጂን መጠቀም ብትጀምርም ይህ ነው የሚባል ለውጥ አለመምጣቱን መናገራቸው የዚሁ የባዮ ቴክኖሎጂ በአገራችን በአግባቡ እየተሰራበት አለመሆኑን አመላካች ነው።
OFAB ደግሞ የተለያዩ ምክክር፣ የውይይትና ስለጠና መድረኮችን የሚያመቻች በመሆኑ ስለ ግብርና ባዮቴክኖሎጂ ዕውቀት ሽግግር ከፍተኛ ጠቃሜታ ያለው መሆኑ ከላይ በጠቀስነው መድረክ፤ ዶ/ር አበራ ዴሬሳ የኢግምኢ ቦርድ ሊቀመንበር እና ዶ/ር ፍሬው መክብብ የብሔራዊ ዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ሶሳይቲ ፕሬዝዳንትን፤ እንዲሁም በባዮቴክኖሎጅ አጠቃቀም እና ባዮቴክኖሎጅ በግብርናው ዘርፍ ስለሚያበረክተው አስተዋጽኦ የተለያዩ ጥናቶችን ያደረጉት (ያበረከቱት) የOFAB የሰሜን ምዕራብ ቀጣና አስተባባሪ እና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ነጋ ብርሃኔን ጨምሮ በሚመለከታቸው መገለፁም እንዲሁ ኢትዮጵያ ከኦፋብ ጋር በመሆን በያዝነው አመት በግብርናው መስክ የተሻለ ውጤት (192 ቢሊዮን ዶላር) ልታስመዘግብ ትችላለች ለሚለው ትንበያ የራሱ የሆነ የማመላከት አቅም አለውና ይብለ የሚያሰኝ ነው።
የሚመለከታቸው በተገኙበት፣ በኦፋብ ፕሮጀክት አነሳሽነት ተካሂዶ በነበረውና በጎንደር ዩኒቨርሲቲና በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ትብብር በባህር ዳር ከተማ በግብርና ባዮቴክኖሎጅ አጠቃቀም ዙሪያ ግንዛቤ የተያዘበት፤ እንዲሁም፣ ከአማራ ግብርና ምርምር የሚመለከታቸው የምርምር ዘርፍ አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች፣ የጎንደር፣ የባህር ዳር፣ የደብረ ማርቆስ፣ የደብረታቦር፣ እንጂባራ ዩኒቨርሲቲ የባዮቴክኖሎጅ ትምህርት ዘርፍ ተወካዮች መገኘታቸው የተነገረለት መድረክ በተካሄደበት ወቅት “የግብርና ምርምር ስራዎች በባዮቴክኖሎጂ ካልተደገፉ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና ተፈላጊውን ለውጥ ለማምጣት አዳጋች ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በግብርናው ዘርፍ ያሉ ተዋናዮች እና ውሳኔ ሰጭ አካላት በባዮቴክኖሎጂ ዙሪያ የተዛቡ አመለካከቶችን በማስተካከል በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡″ እንዲሁም “በቀጣይ ልዩ ልዩ ስልቶችን በመጠቀም በግብርና ባዮቴክኖሎጅ ዙሪያ ለህብረተሰቡ፣ ለውሳኔ ሰጭ አካላትና በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ ተቋማትና ባለሙያዎች የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መሰራት እንዳለበት መግባባት ላይ″ መደረሱና የጋራ ግንዛቤ መያዙም እንደዚሁ ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቷን የሚያመላክት ነው።
በአገራችን ባዮቴክኖሎጂ በተገቢው መንገድ በስራ ላይ ባለመዋሉ ምን ጉዳት አስከተለ?
25 ጁን 2020 “ባዮቴክኖሎጂና የደህንነት ሕይወት ጉዳይ በኢትዮጵያ″ በሚል ርእስ ለንባብ የበቃው የፀጋዬ መኩሪያ ጽሑፍ (ዝርዝሩን ከwordpress.com መመልከት ይቻላል።) እንዳሰፈረው “የባዮቴክኖሎጂ ጽንሰሃሳብ ግንዛቤ በሕዝባችን ዘንድ ሳይፈጠርና ዘርፉ በሕዝቡ ዘንድ በትርጉም ደረጃ እንኳን ሳይታወቅ በመዘግየቱ ምክንያት በሃገሪቱ የግንዛቤና አሰራር ችግሮች ተስተውለዋል።″ በመሆኑም በምርታማነታችን ላይ የራሱን ተፅእኖ ፈጥሯል።
ባጠቃላይ፣ ባቶቴክኖሎጂን ከመጠቀም አንፃር እንደ አህጉር (በ2024 ጂዲፒዋ ገና $3 (ሶስት) ትሪሊዮን ይደርሳል የተባለላት አፍሪካ)ም ሆነ አገር ከፍተኛ ክፍተቶች እንዳሉ በሚገባ ተመልክተናል። ይህም ችግሩን በተቻለ ፍጥነት መፍታት እንደሚገባ ያሳስባል። በተለይ አይኤምኤፍ ከአፍሪካ በ5ኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጣት ኢትዮጵያ በ2024 ጂዲፒዋ $192 ቢሊዮን (40% ከግብርና) ይደርሳል ብሎ ተንብዮአል። ይህ እውን ይሆን ዘንድ (አይቀሬነቱንና አስፈላጊነቱን፤ እንዲሁም፣ የመጪው ዘመን የቴክኖሎጂ የበላይነቱን ከወዲሁ ተገንዝቦ) ባዮቴክኖሎጂን በሚገባ ማልማትና በአግባቡ መጠቀም ለነገ ሊባል የሚችል ጉዳይ አይደለምና፣ እንደ አገርም ሆነ አህጉር ወገብን አጥብቆ መነሳትን ግድ ይላል።
ግርማ መንግሥቴ ጋዜጠኛ ሲሆን በኢትዮጵያ ከ 20 አመታት በላይ በዘርፉ አገልግሏል ( girmaexplore@gmail.com )
