
በህክምናው ዓለም ዘመኑ ካፈራቸውና ከደረሰባቸው ድንቅ የህክምና ጥበቦች አንዱ የኒኩሊየር ህክምና ነው። የኒኩሊየር ህክምና ጨረር አመንጪ መድሃኒቶችን (radiopharmaceutical) በተለያየ ዘዴ ለታካሚው በቀጥታ በመስጠት አብዛኛው የሰውነት ክፍሎችን ለመመርመር የሚያስችል ነው። ይህ የምርመራ አይነት በሌሎች የህክምና መመርመሪያ ዘዴዎች (በቤተ-ሙከራ / Laboratory፣ በራዲዮሎጂ /CT scan, MRI … etc/ ምርመራዎች) ማግኘት የማንችላቸውንና የተደበቁ በሽታዎችን ለማግኘት የሚያስችል ነው።
ይህ የህክምና ዘዴ ከመመርመር ባለፈ ደግሞ አንዳንድ ህመሞችን (የእንቅርት በሽታን፣ በካንሠር የተጎዳ ህዋስ በቀዶ ጥገና ከወጣ በኋላ የካንሰሩ ህዋሶች ወደ ሌላ የሰውነት ክፍል እንዳይሰራጩ ባሉበት በጨረር ለመግደል … ወዘተ) ቀጥታ ህክምና ለመስጠት እንደሚያስችል የሚናገሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በውስጥ ደዌ ህክምና ክፍል የኒኪሊየር ህክምና ክፍል ኃላፊ እና በሙያቸው ደግሞ የኒኩሊየር ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ቤቴልሔም ወርቁ ናቸው።
እንደ ዶክተር ቤቴልሔም ማብራሪያ፤ ኒኩሊየር ህክምና የሰውነት ክፍሎችን ወይም የህዋሶችን የአሠራር ሥርዓት የሚመረምር ነው። ይህም ከሌሎች የመመርመሪያ ዘዴዎች ልዩ ያደርገዋል። የኒኩሊየር ህክምና አንድ የሰውነት ክፍል ቅርጹን ከመቀየሩና በገጠመው እክል ከመጎዳቱ አስቀድሞ የአሠራር ሥርዓቱ ላይ ችግር ሲያጋጥም ቀድሞ ለማወቅ ያስችላል። በዚህም አንድ የሰውነት አካል አሠራሩን መርምሮ ችግር ካላ ሳይጎዳ በፊት ለማከም ያስችላል።
የኒኩሊየር ህክምና መድሃኒቶቹ ጨረር የሚያመነጭ አካልና ለመድሃኒትነት የሚውል ክፍል አላቸው። ለአብነት አንድ የኒኩሊየር መድሃኒት ለኩላሊት ምርመራና ህክምና ከታሰበ መድሃኒቱ ኩላሊት ዘንድ በተለያዩ መንገዶች (በደም ስር፣ በትንፋሽ፣ በሚዋጥ እንክብል መድሃኒት መልክ ወዘተ) እንዲደርስ ይደረጋል። በዚህም ጨረሩ ቀጥታ ወደ ታካሚው ገብቶ ከውስጥ ወደ ውጭ በመውጣት የታካሚውን የሰውነት ክፍል ያሳያል። በተቃራኒው የራዲዮሎጂ ምርመራዎች ደግሞ ጨረሩ ከውጭ ወደ ውስጥ በመግባት ነው የታካሚውን የተጎዳ ክፍል የሚያሳዩት።
ስለዚህ ወደ ታካሚው ኩላሊት የተላከው የኒኩሊየር ህክምና ጨረር ከውስጥ ወደ ውጭ ኩላሊትን ሲያሳይ፤ በተለያዩ ቴክኖሎጂ መረጃው በምስል ጭምር ተደግፎ ይወሰዳል። ይህ መረጃና ምስል ኩላሊት ምን ችግር አለባት? የአሠራር ሥርዓቷ ጤነኛ ነው ወይስ ተዛብቷል? በጥሩ ጤንነትና ሁኔታ ትገኛለች ወይ? በደንብ ትሠራላች ወይ? እያጣራች ነው ወይ? … የሚለውን ነገር ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፤ ለሀኪሙ መረጃ ይሰጣል። በተመሳሳይ መንገድ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች (አጥንት፣ ጭንቅላት፣ ልብ፣ ጉበት …) የአሠራር ሥርዓታቸው ላይ ምርመራ በማካሄድ በሌሎች የመመርመሪያ ዘዴ ያልተገኙና የተደበቁ በሽታዎችን መርምሮ ለማግኘት ያስችላል።
በተለይ የካንሰር ህመም ስር ከመስደዱና ከፍተኛ ደረጃ ከመድረሱ አስቀድሞ በሽታውን ለማወቅና ተገቢውን ህክምና ለመስጠት ወይም ታካሚው ተገቢውን ህክምና እንዲያገኝ ይረዳዋል። እንዲሁም አንድ ሰው ኩላሊቱን ለሌላ ሰው ለመለገስ ሲያስብ ለጋሹ አካል የኩላሊቱን ሁኔታ ቅድሚያ ማወቅ አለበት። በመሆኑም የቀኝም ሆነ የግራ ኩላሊቶቹ ምን ያህል እንደሚሠሩ ምርመራ ለማድረግ በዋነኝነት የኒኩሊየር ህክምና ወሳኝ ነው።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ አንዳንድ ህመሞች ላይ ቀጥታ ህክምና ለመስጠት ያስችላል። በተለይ ደግሞ አንድ ሰው እንቅርት ኖሮበት እንቅርቱ ከፍተኛ ሆርሞን የሚያመነጭ ከሆነ፤ በቀዶ ህክምና እንቅርቱን (toxic multinodular goiter) ማውጣት ሳያስፈልግ በጨረሩ ተመሳሳይ ህክምና መስጠት ይቻላል። በጥቅሉ የኒኩሊየር ህክምና ከሌሎች ለየት የሚያደርገው ምርመራም ያደርጋል፤ ህክምናም ይሰጣል። ህክምናውም ለአብዛኛው ታካሚዎች አስፈላጊና ጠቃሚ እንደሆነ ዶክተር ቤቴልሔም ያስረዳሉ።
(ምንጭ : አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ህክምን ሳይንስ ኮሌጅ)
