
በመኮንን ተሾመ
(ጋሞ ዞን ፣ አርባ ምንጭ) ፡ የማንጎ ነጭ ግግር ተባይ (White Mango Scale Pest) ወደ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2001 እና 2002 “አልፋንሶ” የተባለ የህንድ የማነጎ ዝርያ በገባበት ወቅት ነበር የገባው። አዲሱን የማነጎ ዝርያ ወደ ኢትዮጵያ ያስገባዉ ግሪን ፎከስ ኢትዮጵያ ሊሚትድ የተባለ የህንድ የግል እርሻ ኩባንያ ነው።

ኩባንያዉ በምርታማነቱና ጣዕሙ የተሻለ ነዉ ያለዉን የ“አልፋንሶ” ዝርያ በማስገባትና በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ጉቶ ጊዳ ወረዳ ላኮ ቀበሌ ተክሎ ጥሩ ምርት ለማግኘት አስቦ ነበር።
ይሁንና ተባዩ በጉራፈረዳ ወረዳ ሰቃ እርሻ አካባቢና ሌሎችም አካባቢዎች በኋላም በሀገሪቱ ምዕራብ ፣ መካከለኛና ደቡብ አካባቢዎች በመስፋፋት በነባሩ የኢትዮዽያ ማንጎ ላይ ከፍተኛ የመጥፋት አደጋ ደቀነ። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ማንጎ ቅጠሉንም ፍሬዉንም በሚጎዳዉ የማንጎ ነጭ ግግር ተባይ ምክንያት ምርት መስጠት ተስኖት ከነጭራሹ የመጥፋት አደጋም ተጋርጦበታል።

ይህንን የማንጎ የወረርሽኝ ሀገራዊ አደጋ የተረዱት የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ እና የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እየተጠናቀቀ ባለዉ የበጀት አመት ማንጎን ከመጥፋት የማዳን አላማ ያለዉ የምርምር ስራ በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ በሚሌ ጫሞ የደቡብ ክልል ንዑስ የግብርና ምርመር ጣቢያ ጀምረዋል።
በአርባምንጭ ከተማ የእጽዋት ጤና ተቋም የሚሰራዉ ምርምር በባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የገንዘብ ድጋፍ እና በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የምርምር ቴክኒካዊ ስራ ነው።
ባለፈዉ ሳምንት ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ∙ም∙ ከባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና ከአጋር ድርጅቶች የተዉጣጡ ባለሞያዎችና አመራሮች በምርመር ጣቢያዉ እየተሰራ ያለዉን ስራ ጎብኝተዋል።

አቶ ባልጣ በገጄ በደቡብ ኢትዮዽያ ክልል ፣በጋሞ ዞን የምዕራብ አባያ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደር በአደገኛዉ የማነጎ ተባይ ምክንያት ያገኙት የነበረዉ ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ ሲሆን ሁኔታዉም በኑሮአቸዉ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን በወቅቱ ተናግረዋል።
አቶ ባልጣ የማንጎ ተክላቸዉን ወረርሽኙ ከማጥቃቱ በፊት የማንጎ ምርት ወደ አዲስ አበባ ገበያ በአይሱዙዎች እያስጫኑና እየሸጡ ጥሩ ገበያ ያገኙ እንደነበር አስታዉሰዉ ባለፉት ጥቂት አመታት ግን በነጭ ማንጎ ስኬል ምክንያት የማንጎ ተክሎቻቸዉ ምንም አይነት ምርት ስላልሰጡዋቸዉ ምንም አይነት ገቢ አላገኙም።
እንደሳቸዉ ገለፃ በሚኖሩበት አካባቢ ብዙ የማንጎ አምራቾች በበሽታዉ አደገኛነትና ምርት ማጣት ተማረዉ ማንጎዎቻቸዉን እየነቀሉ በሌላ አዝዕርት እየተኩ ነዉ።
አቶ ባልጣ ግን እስካሁን ተስፋ ባለመቁረጥና በወረዳቸዉ የሚገኙትን የግብርና ባለያዎችን ምክር በመጠየቅ መፍትሄ ለማግኘት እየሞከሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
በመሆኑም ከወረዳቸዉ የግብርና ባለያዎችን በሽታዉን የመቋቋ አቅም ያላቸዉን የማንጎ ዝርያዎች ለማግኘት በመሞከርም ላይ እንዳሉ በባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ድጋፍ የመጣዉ ወረርሽኙን የመከላከል የምርምር ስራና ተስፋ እንደሰጣቸዉ ገልፀዋል።
የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ካሳሁን ተስፋዬ እንደሚያስረዱትም በተቋማቸዉ የገንዘብ ድጋፍ የተጀመረዉ ማንጎን የማዳን የምርምር ስራ በአዳማ ሳይንስና ቴክሎሎጂ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት በአጭር ጊዜም ተስፋ ሰጪ ዉጤት የተገኘበትም ነዉ።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ አዲሱ የምርምር ፕሮጄክት በዋነኝበት በኢትዮጵያ በማነጎ ነጭ ግግር ተባይ የተጠቁ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የማነጎ ተክሎችን ከግንዳቸዉ ላይ ዝቅ ብሎ በመቁረጥ ለዘመናት በመሬት ዉስጥ ስር ሰዶ ከአካባቢ የተስማማዉ ግንዱ ላይ ሌሎች የማንጎ አዳዲስ ዝንጣዮችን ከአናቱ ላይ በተገቢዉ መንገድ በማገናኘትና በመትከል ∕ Grafting∕ ዘዴ የሚተገበር ነዉ።
ፕሮፌሰር ካሳሁን አክለዉም በተቆረጡ ማንጎዎች ግንድ ላይ አዳዲስ ማንጎዎችን የማልማት ስራዉ ሁለት ዋና ዋና ጥቅሞች ይኖሩታል።
እንደሳቸዉ ገለፃ አንደኛዉ ጥቅም ከማነጎ ነጭ ግግር ተባይ በሽታ ነፃ የሆኑ ማንጎዎችን መልሶ ማልማት ሲሆን ሁለተኛዉ ጥቅም ደግሞ እስከ 40 ሜትር እርዝመት ያላቸዉንና ለእንክብካቤና ምርት አሰባሰብ የማይመቹ ዝርያዎችን በመግረዝና በፀረ-ተባይ በማከም በሰዉ ቁመት ልክ አጠር ብለው ፍሬ እንዲሰጡና ለእንክብካቤ እንዲመቹ ማድረግ ነዉ።
[የፕሮጄክቱ] …አንደኛዉ ጥቅም ከማነጎ ነጭ ግግር ተባይ በሽታ ነፃ የሆኑ ማንጎዎችን መልሶ ማልማት ሲሆን ሁለተኛዉ ጥቅም ደግሞ እስከ 40 ሜትር እርዝመት ያላቸዉንና ለእንክብካቤና ምርት አሰባሰብ የማይመቹ ዝርያዎችን በመግረዝና በፀረ-ተባይ በማከም በሰዉ ቁመት ልክ አጠር ብለው ፍሬ እንዲሰጡና ለእንክብካቤ እንዲመቹ ማድረግ ነዉ።

በወረርሽኙ የተጠቁ የማንጎ ዛፎች ተቆርጠዉ በነሱ ላይ የሚተከሉት እሰከሚደርሱ ድረስም ለማንጎ አብቃይ አርሶ አደሮች አማራጭ የገቢ ምንጭ የሚሆኗቸዉ በርበሬ ፣ዝንጅብል እና ቁንዶ በረበሬ ያሉ አማራጭ ምርቶችን ከማንጎዉ ልማት ጎን ለጎን (Inter-Crop) በማካሄድም አርሶ አደሮችን ለመደገፍም በምርምር ፕሮጄቱ እየተሰራ መሆኑንም ፕሮፌሰር ካሳሁን አስታዉቀዋል።
ፕሮፌሰር ካሳሁን እንደጠቆሙት በተቋማቸዉ የተጀመረዉ ማንጎን የመታደግ የምርምር ስራ ተስፋ ሰጪ ሲሆን ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆንና በሀገር ደረጃ ትርጉም ያለዉ ስራ እንዲሰራና የሀገሪቱን ማንጎ ማዳን እንዲቻል ሁሉም የሚመለከታቸዉ የመንግስት ፣ የምርምር እና የትምህርት ተቋማት በንቃት መሳታፍ አለባቸዉ።

በማንጎ ነጭ ግግር ተባይ ላይ የሚደረገዉ ምርምር ዋና ተመራማሪ የሆኑት የአዳማ ሳይንስና ቴክሎሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶ⁄ር ኦፍጋ ጂራታ በበኩላቸዉ ምርምሩ በአይነቱ አዲስ እንደመሆኑ የተወሰኑ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙም ነባር የማንጎ ዛፎችን በመቁረጥ አዳዲስ ዝንጣዮችን በላያቸዉ ላይ የማልማቱ ጅምር ምርምር የተሳካ እነደሆነ አስረድተዋል።
በምርምሩ ከወረርሽኙ ነፃ የሆኑና ቁመታቸዉም ለእንክብካቤና ምርት ለመሰብሰብ የተመቹ ማንጎዎችን እንደገና ማልማት እንደሚቻል መረጋገጡን የተናገሩት ዶ⁄ር ኦፍጋ የተሰራዉ ሰራ በተወሰኑ በወረርሽኙ በተጠቁ ዛፎች ላይ በመሆኑ የተገኙትን የምርምር ዉጤቶች ለማስፋት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ በመስራት ስራዉ ቀጣይነት እንዲኖረዉ መደረግ አለበት ብለዋል።

በግብርና ሚኒሰቴር እፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ንጉሴ በወቅቱ በሰጡት አስተያየት በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ የእፅዋት ተባዮች በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች እየተስፋፉ መምጣታቸዉን ጠቁመዉ በእፅዋት ጥበቃ ላይ በሀገር ደረጃ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አስታዉሰዋል።
አቶ በላይነህ እንዳሳሰቡት ከሆነ ከዉጪ አገር ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ስነ-ህይወታዊ ሀብቶችን በተመለከተ የ‹‹ኳራታይን›› ስራ ክፍተት በመኖሩ ምክንያት ክፍተት ተፈጥሯል።
በመሆኑም የስነ-ህይወታዊ እንቅስቃሴ ከዉጪ አገር ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ብቻም ሳይሆን ከገቡም በኋላ በሀገር ዉስጥ የሚኖሩ እንቅስቃሴዎችም ከፌዴራል ተወካዮች ምክር ቤት ጀምሮ በየደረጃዉ ባሉ የክልል እና አገር አቀፍ ህግ አዉጪ እና ህግ አስፈፃሚ አካላት የ‹‹ኳራታይን›› ስራ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር መደረግ አለበት ሲሉ አቶ በላይነህ ተናግረዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ አካባቢ አርሶ አደር የሆኑት አቶ ሞሃመድ አሊ እንደሚሉት ከቅርብ አመታት ወዲህ በማነጎ ነጭ ግግር ተባይ ምክንያት እሳቸዉና ሌሎች በክልልሉ የሚኖሩ የማንጎ አምራች አርሶ አደሮች ምርት ሊያገኙ አልቻሉም።
ይሁንና በወቅቱ በተገኙት የመንግሰት ሀላፊዎችና የግብርና ባለሞያዎች ተደጋግሞ እንደተነገረው የማንጎ ተክል የአርሶ አደሩ የኢኮኖሚ ምንጭ ፣ የማህበራዊ ጉዳይ መመካከሪያ ጥላ እና ከአየር ንብረት ተፅዕኖ መከላከያ በመሆኑ ለማህበረሰቡ ጠቀሜታው እጅግ ከፍተኛ ነው።
በመሆኑም አቶ ሞሃመድ አዲሱ የማንጎ ምርትን ለመሰብሰብ የማይመቹ ዝርያዎችን በፀረ-ተባይ በማከምና በመግረዝ በሰዉ ቁመት ልክ ሆነዉ ፍሬ እንዲሰጡና ለእንክብካቤ እንዲመቹ እንዲሁም ከበሽታ ነፃ የሆኑ የማንጎ ዛፎችን የማልማት የምርምር ሰራዉ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንዲስፋፋ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
አቶ ሞሃመድ በአርባ ምንጭ ያዩትን አበረታች የምርምር ስራም ለሌሎች አርሶአሮች ለማስተላለፍና ለማስተማር ቃል ገብተዋል።
በሀገራችን ከፍተኛ የህግ አዉጪ የሆነዉ የተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በወቅቱ በሰጡት የስራ ማሳሰቢያ በሀገራችን ያለዉን የማንጎ ሀብት ጨምሮ ሌሎችንም የተፈጥሮ ሀብቶች ፣ የሰዉ ሃይል እና ቴክኖሎጂ በአግባቡ በመጠቀምና በመምራት ልማትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናገረዋል።
የተጀመረዉን ማንጎን ከመጥፋት የማዳን የምርምር ስራም የአካባቢ ደህንነትን በጠበቀ ምልኩና ስፋት ባለዉ መልኩ ማስቀጠል እንደሚገባም አሰታዉቀዋል።
እስካሁን ለተገኘዉ ዉጤትም የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን ፣ የአዳማ ሳይንስና ቴክሎሎጂ ዩኒቨርሲቲን እና ሌሎች በንቃት የተሳተፉ ተቋማትን እና ግለሰቦችንም አመስግነዋል።
