
በ መኮንን ተሾመ
የኢትዮጵያ የሕብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት የተመሰረተበትን የአንድ መቶ አመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ ክብረ በዓል በመጪዉ ህዳር ወር 2017 ዓ∙ም∙ በደማቅ ሁኔታ ሊያከብር እንደሆነ አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ይህን ያስታወቀዉ ዛሬ ባካሄደዉ የአንድ መቶ አመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ ክብረ በዓል የማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ ነዉ።
የክብረ በዓል የማስጀመሪያ ፕሮግራሙ የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች እንዲሁም የሌሎች አጋር አካላት ተወካዮች በተገኙበት በዛሬዉ እለት በተቋሙ የስብሰባ አዳራሽ የተከናወነ ሲሆን ለበዓሉ የተዘጋጀው ልዩ የመረጃ ድረ-ገጽ https://anniversary.ephi.gov.et/ በይፋ ተመርቆ ስራ ጀምሯል።
በተጨማሪም በወቅቱ ከአልማዝ ኢዩቤልዩ ክብረ በዓል ጋር በተያያዘም አብሮ ለሚካሄደዉ የኢንስቲትዩቱ 5ኛ ሳይንሳዊ ጉባኤ (5th EPHI Scientific Conference) የሚቀርቡ የምርምርና ጥናታዊ ጽሑፎች በድረ-ገጽ ብቻ ለዉድድር የሚቀርቡበት፣ የሚገመገምበትና ውጤትም የሚገለፅበት በየነ መረብም ይፋ ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያ የሕብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በፕሮግራሙ ማስጀመሪያ ላይ እንደተናገሩት የአልማዝ ኢዩቤልዩ ክብረ በዓሉ የኢንስቲትዩቱ የምዕተ-ዓመት የሕብረተስብ ጤና አገልግሎቱ የሚንፀባረቅበትና የወደፊቱ ወሳኝ ሚናዉም የሚታይበትና የሚታቀድበት አጋጣሚ ነዉ ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት በርካታ የሕብረተስብ ጤናን የተመለከቱ ጥናትና ምርምሮችን፣ የላብራቶሪ አገልግሎቶችን፣ የማሕበረሰብ ጤና አደጋዎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎችንና እና ሌሎች ተያያዥ ተልዕኮዎችን ሲወጣ የነበረ በመወጣት ላይ ይገኛል።
“በዚህ አስደሳች በዓል ወቅት የኢንስቲትዩታችንን ታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናይ በርካታ እውቀታቸውን ያበረከቱ እና ለሀገራችን ጤና መሻሻል እራሳቸዉን አሳልፈዉ የሰጡ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ግለሰቦች ባስመዘገቡት አስደናቂ ስኬት እንኮራለን።”ብለዋል
እንደሳቸዉ ገለፃ በአሁኑ ወቅትም ተቋሙ የሥራ አድማሱን በማስፋት በሀገር አቀፍ ደረጃ ልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ጤና ነክ ስራዎችን በስፋትና በጥራት እንዲሁም በቅንጅት እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ተቋሙ በአፍሪካ ቀዳሚ የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ለመሆን እየሰራ ይገኛል።
ዶ/ር መሳይ እንዳሉት ላለፋት 1ዐዐ አመታት ኢንስቲትዩቱ የሀገሪቷ የሕብረተሰብ ጤና ጉዳዮች ምሶሶና ማዕከል በመሆን የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ ሲያበረክት ነበር፡፡
”በአሁኑ ጊዜም ኢንስቲትዩቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በመቆጣጠር፤ ጥራቱን የጠበቀ የላብራቶሪ አገልግሎት በመስጠት፣ በሕብረተሰብ ጤናና በስነ-ምግብ ዙሪያ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ፣ በጤና ነክ መረጃዎች ትንተናና ቅመራ ዙሪያ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉን አቀፍ የአንድ ጤና እና የአለም አቀፍ የጤና ደህንነት መርሐ ግብር በማስተባበርና በመምራት ብሎም የኢፒዲሞሎጂን ስልጠናዎችን እና ሊሎች ተያያዥ የሆኑ የሕብረተሰብ ጤና ነክ የሆኑ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡” ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አክለዉ ተናግረዋል።
የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ በወቅቱ ስለ ኢንስቲትዩቱ የ1ዐዐ ዓመት በአል አከባበር እንዲሁም ስለተቋሙ አነሳስና ታሪክ ለእንግዶች ገለፃ አድርገዋል፡፡
ዶ/ር ጌታቸው አክለዉም ተቋሙ ከ1924 ዓ.ም ጀምሮ ባደረገው ጉዞ ለምርምርና ለቴክኖሎጂ ሽግግር የነበረዉ ያልተቋረጠ አስተዋፅኦ የህብረተሰብ ጤናን በማሳደግ ረገድ ለስኬታችን መነሻ ምክንያት ነው ብለዋል።
“ለተልዕኳችን መሳካት ድጋፍ ላደረጉልን ሁሉ ያለኝን ጥልቅ ምስጋና አቀርባለሁ። የናንተ የሁላችሁም ትብብር ለስኬቶቻችን ወሳኝ ነበር፣ እና የህዝብ ጤና ምርምር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እድገትን እያሳካን ስንቀጥል አዳዲስ መንገዶችን በጋራ ለመተለም እያሰብነ ነዉ።” ሲሉም ለተሳታፊዎች ገልፀዋል።
የክብረ በዓል የማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ በወቀቱ የተገኙት የአርመር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና የኢትዮጵያ የሕብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት የቀድሞ ተመራማሪ ኘሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸዉ የኢትዮጵያ የሕብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት በሀገሪቱ ታሪክ በጣም ረጅም ታሪክ ያለዉ የስኬት ዘመን ያሳለፈ እንደሆነና በዚህ ደረጃ በኢትዽያም በሌሎች አፍሪካ ሀገራትም ለረጅም አመን ያገለገለ ተቋም ማግኘት አዳጋች መሆኑን አዉሰተዋል።
የመቶ አመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ ክብረ በዓሉም ያለፉትን ተሞክሮዎች ለመቀመርና ለወደፊቱም ያለዉን ተሰፋና ስጋቶች ለይቶ በስኬታማነት ለመጓዝ የሚያግዝ ይሆናል ብለዋል።
ኘሮፌሰር አፈወርቅ ኢንስቲትዩቱ ላለፋት 1ዐዐ ዓመታት በሕብረተሰብ ጤና ዙርያ ላበረከተዉ ከፈተኛ አሰተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበው ከሳቸዉ ተቋም ጋር ትብብሮች ሲያደርጉ እንደነበረውም ተናገረዉ ለወደፊቱም ትብብሩ የሚጠናከር መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
