
በመካከለኛው፣ በምሥራቅና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊኖር ስለሚችል፤ የደረሱ ሰብሎችን በመጪዎቹ 10 ቀናት መሰብሰብ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳስቧል።
ኢንስቲትዩቱ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በመካከለኛው፣ በምስራቅ እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል።
ይህም ሁኔታ በደረሱ ሰበሎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ጥንቃቄና ዝግጅት በማድረግ የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ ተግባር ማከናወን ይኖርባቸዋል።

በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚኖረው እርጥበት በተለያየ ምክንያት ዘግይተው ለተዘሩና የእድገት ጊዜያቸውን ላልጨረሱ የመኸር ሰብሎችም ሆነ ለቋሚ ተክሎች የተሟላ እድገት የሚያስፈልጋቸውን የውሃ አቅርቦት ከማሟላት አንፃር አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረውም በመግለጫው አመልክቷል።
በደቡብ ምዕራብና በደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተስፋፋና ሰፊ ቦታዎችን የሚያካትት ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን የሚኖረው ዝናብ ውሃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች የሚገኘውን የዝናብ ውሃ ለማቆርና ለመያዝ መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል።

ነገር ግን በተዳፋትና ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የአፈር መሸርሸርና በእርሻ ማሳዎች ላይ የውሃ መተኛት ሊያግጥም እንደሚችል መግለጫው ጠቁሞ፤ አርሶ አደሮችና የሚመለከታቸው አካላት ከወዲሁ በግብርና ባለሙያዎች በመደገፍ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ መግለጫው አሳስቧል።
በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበጋ ወቅት እርጥበት ተጠቃሚ በሆኑት የባሮ አኮቦ፣ ገናሌ ዳዋ፣ በመካከለኛውና በታችኛው ኦሞ፣ ጊቤ፣ ዋቢሸበሌ የታችኛው ስምጥ ሸለቆ እና ኦጋዴን፣ ተፋሰሶች ላይ የተለያየ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚያገኙ ይጠበቃል ነው ያለው መግለጫው።
ይህም ሁኔታ የተፋሰሶችን የገጸ ምድርም ሆነ የከርሰ ምድር የውሃ ሀብት ከማበልጸግ አንጻርም ሆነ በተለያየ ዘዴ ለሚከናወኑ የውሃ ማሰባሰብ ተግባራት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው መግለጫው አንስቶ፤ የበጋ እርጥበት ተጠቃሚ ባልሆኑት ተፋሰሶች ላይ የሚጠበቀው እርጥበት የተሻለ የውሃ ሀብት በግድቦችና በውሃ አካላት ላይ እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደርጋል መባሉን ኢፕድ ዘግቧል።
በሁለተኛው አስር ቀናትም ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በደቡባዊው አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች በመነሳት ሰፊ ቦታዎችን የሚያካትትና ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ ይላል መግለጫው።
በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ትንበያዎች የሚያመላክቱ መሆኑን ገልጾ፤ ይህም ሁኔታ ለአርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለአረንጓዴ እፅዋት ልምላሜ ሽፋን መሻሻል፣ ሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ ምንጮችን ከማጎልበት እና የውሃ አቅርቦትን ከማረጋገጥ አንፃር አዎንታዊ እንደሚኖረው በመግለጫው አስታውቋል።

