
የእብድ ውሻ በሽታ
በመኮንን ተሾመ
የእብድ ውሻ ህመም ሊሳ ቫይረስ (Lyssavirus) በተሰኘዉ በሽታ አምጪ ተዋሲያን በተጠቁ እንስሳት ንክሻ ማለትም በውሻ፣ ቀበሮ፣ ተኩላና በሌሎች ወደ ጤናማ ሰው ሊተላለፍ የሚችል አደገኛ የጤና እክል ነው፡፡
በሽታዉ በታሪክ ከታወቁትና በጣም ጥንታዊ ከሆኑ በአለማችን ከ 4000 ዓመታት በፊት ከታዩ የጤና ችግሮች አንዱ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይሁንና እንደ የኢትዮዽያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሆነ በሽታዉ አሁንም በኢትዮጵያ አሳሳቢ የሕብረተሰብ ጤና ጉዳይ ነዉ።
የኢንስቲትዩቱ የባክቴሪያል፣ ፓራሳይቲክ እና የእንስሳት ነክ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት በአዳማ ከተማ በዚህ ሳምንት (ከጥር 6-8/2016 ዓ.ም) ባዘጋጃው ስልጠና ላይ እነደገለፀዉ ከሆነ የእብድ ውሻ በሽታ አሁንም በገሪቱ አሳሳቢ የሕብረተሰብ ጤና ጉዳይ በመሆኑ ችግሩ ጨርሶ እስኪወገድ ድረስ የሁሉም አካላት ትብብርና እርብርብ ያስፈልጋል።
እንደ ኢንስቲትዩቱ ድረ-ገፅ ከሆነ ስልጠናውን በዋናነት ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመተባበር ያዘጋጃው UK Health Security Agency (UKHSA) ሲሆን ስልጠናው የተሰጠው ከአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ አማራ፣ ሶማሌ እና ትግራይ ክልሎች ለተውጣጡ የጤና ኤክስቴሽን፣ የእብድ ውሻ በሽታ ክትባት እና የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች ነበር።

ዶ/ር ይመር ሙሉጌታ የዳይሬክቶሬቱ ከፍተኛ ተመራማሪ እና የእንስሳት ነክ በሽታዎች ቡድን መሪ እንደተናገሩት ስልጠናው የኢንስቲትዩቱ እና የእብድ ውሻ በሽታ መከላከል ቴክኒካል ኮሚቴ እንዲሁም በብሔራዊ አንድ ጤና የ2016 ዓ.ም የተግባር ዕቅድ ውስጥ የተያዘ ነው። ይህም በ 2030 የእብድ ውሻ በሽታን ፈጽሞ ለማጥፋት ወይም ዜሮ የሞት ሪፖርትን ለማሳካት የሚያስችል ሀገራዊ አቅምን ለመገንባት ነው ብለዋል።
የUKHSA ተወካይ ዶ/ር ባየህ አሸናፊ ስለ ስልጠናው አጠቃላይ ዓላማና ከስልጠናውም ምን እንደሚጠበቅ ከገለፁ በኋላ ለሰልጣኞች የቅድመ ስልጠና ፈተና ተሰጥቷል።
የእብድ ውሻ በሽታ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ በዶ/ር ይመር የቀረበ ሲሆን ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ጥናቶችም በግብርና ሚኒስቴር፣ ከኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር እና የክትባት ምርት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸው ሠልጣኞችም በቡድን በቡድን በመሆን ተወያይተው በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መደረግ ስላለባቸው ነገሮች ለተሳታፊዎች አቅርበዋል።
የባክቴሪያል፣ ፓራሳይቲክ እና የእንስሳት ነክ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ገረመው ጣሰው ስልጠናው በየደረጃው መቀጠል እንዳለበትና ሠልጣኞች የሰለጠኑትን ወደሚሄዱበት ቦታ በመወስድ ለሌሎች ማካፈልና በታቻላቸው መጠንም ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መጀመር እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
በመጨረሻም ለሰልጣኞች የእውቅና ሰርተፍኬት እና የባለብዙ ዘርፍ የእንስሳት በሽታዎች ወረርሽኝ ምርመራ መመሪያ (Multisectoral Zoonotic Disease Outbreak Investigation Guideline) መጽሐፍ ተሰጥቷቸዋል።


የእብድ ውሻ በሽታ ምልክቶች
በእብድ ውሻ በሽታየተያዘ እንስሳ የተለየ ጸባይ ማሳየት ይጀምራል፤ በተለይ የመቅበጥበጥና መበሳጨት ምልክት ያሳያል፤ አረፋ ይደፍቃል፣ መብላት ወይም መጠጣት አይችልም፣ አንዳንድ ጊዜ ያለምክንያት በመበርገግ ያገኘውን ሰው ወይም እንስሳ መንከስ እንዲሁም የለሃጭ መዝረብረብ ያሳያል፡፡
የቅድሚያ ምልክቶቹ ትኩሳት እና በተነከሱበት ቦታ ማሳከክ ወይም ማቃጠልን ያካትታል፤እነዚህ ምልክቶች ኃይል የታከለባቸው የሰውነት እንቅስቃሴዎች፣ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ መሸበር፣ የውኃ ፍራቻ፣ የሰውነት ክፍልን ለማንቀሳቀስ መቸገር፣ ግራ መጋባትና ህሊናን መሳት ምልክቶችን አስከትለው ይመጣሉ፡፡
ምልክቶቹ ከታዩ በኋላ የእብድ ውሻ በሽታ በአብዛኛው ሞትን ያስከትላል፤በዚህም በበሽታው የተያዘ እንስሳ ከ5 እስከ7 ባሉት ቀናት ውስጥ ለህልፈት ሊዳረግ የሚችልበት ሁኔታን ሊያጋጥም ይችላል፡፡
በሰዎች ላይ የሚታየው ምልክት ደግሞ ግለሰቡ ንቁ ቢሆንም ቁጡ ይሆናል፣ የብርሃን ጥላቻም ስለሚያድርበት ጨለማን ይመርጣል፣ በድንገት የመበርገግ ጸባይ ይታይበታል፤ በመጨረሻም አቅሉን ስቶ አረፋ እየደፈቀ ለሞት ይዳረጋል፡፡
የእብድ ውሻ በሽታ ወደ ሰዎች የሚተላለፈው በአበደ ውሻ ንክሻ ወይም በሌሎች በተለከፉ እንስሳት እንደመሆኑ በበሽታው የተበከለ እንስሳ ሌላ እንስሳ ወይም ሰው ሲቧጭር ወይም ሲናከስ የእብድ ውሻ በሽታ ሊያስተላለፍ ይችላል።
የተበከለ እንስሳ መራቅ ካልተቻለ ወይም የሰውነት ፈሳሽ አመንጭ ህዋስ ያሉበት ማስተላለፊያ ጋር ከተነካካ የእብድ ውሻ በሽታ ሊተላለፍ ይችላል።
አብዛኛዎቹ በሰዎች ላይ የተከሰቱ የእብድ ውሻ በሽታዎች መንስኤያቸው የውሻ ንክሻ ነዉ፡፡

በሽታውን የመከላከያ መንገዶች
እንደ የኢትዮዽያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሆነ የበሽታው የመከላከያ መንገዶችም ከፍተኛ ተጋለጭነት ላለባቸው ሰዎች ለበሽታው ከመጋለጣቸው በፊት አስቀድሞ የመከላከያ ክትባትን መስጠት ይጠቀሳል፡፡
መወሰድ ያለበት ጥንቃቄም በአበደ ውሻ ወይም በሌላ ማንኛውም እንስሳ የተነከሰውን ወይም የተቧጨረውን ቦታ ለ15 ደቂቃ በውኃ እና በሳሙና ማጠብ፣ በአዮዲን ወይም በሌሎች የንጽህና መጠበቂያ ፈሳሾች ማጠብ ቫይረሱን ሊያስወግድ ይችላል፡፡
በተጨማሪም በሽታውን ለመከላከል ውሾችን በየጊዜው ማስከተብ፣ ከተነከስን ደግሞ በጤና ማዕከላት የሚሰጠውን ክትባትና ተያያዥ ሕክምና በጊዜ መውሰድ ይገባል፡፡
በሽታውን ለመከላከል ቀላሉና ወሳኙ አማራጭ በውሾች ላይ የሚወሰደው ቁጥጥር ነው፡፡ የውሾች ቁጥጥር ሲባል ውሾችን በወቅቱ ተከታትሎ ማስከተባና የውሾችን ቁጥር ሊኖር ከሚገባው መጠን በልጦ እንዳይገኝ መቆጣጠር ማለት ነው፡፡
ውሻን የሚያሳብደውን በሽታ መቆጣጠሪያ መንገዶች ወይም ዘዴዎች በተለይ የውሾች ቁጥጥር በተመለከተ የሚከተሉትን 7 ነጥቦች መሠረት መደረግ አለባቸው፡- በበሽታው የተጠረጠረ ውሻን ለሚመለከተው ክፍል በፍጥነት መጠቆም፡ – የበሽታን ምልክት ያሳየ፣ ያበደ ወይም የተጠረጠረን ማንኛውም እንስሳ ሕብረተሰቡ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ አለበት፡፡ ይህም ሕብረተሰቡን በድንገት ለበሽታው ከመጋለጥ ያድናል፡፡
ባለቤት የሌላቸውን ውሾች እንቅስቃሴን መግታት፡ –
ቆየት ካሉ የበሽታውን የመከላከያ ዘዴዎች ውስጥ አንዱ ውሾችን እንዳይዘዋወሩ ማሰር ነበር፡፡ የውሾችን የእርስ በርስ ግንኙነት ማገድና በመኖሪያ ቤታቸው አስሮ ማቆየት የበሽታውን ስርጭት መቀነስ ያስችላል፡፡ ሆኖም ግን አንዳንድ ጊዜ በቤታቸው ታስረው የሚጠበቁ ውሾች በበሽታው ተይዘውበሰዎችና በሌሎች እንስሳት ላይ ችግር ሲፈጥሩ ይታያሉ፡፡ በሕብረተሰቡ ውስጥ ካሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች ውስጥ አንዱ “ታስሮ የሚውል ውሻ በጭራሽ በሽታው ሊይዘው አይችልም” ብሎ ማመን ነው፡፡
ከውሻ ሌላ በበሽታው ሊጠቁ ከሚችሉ እንስሳት ውስጥ ድመትና ሸለመጥማጥ በቀላሉ አጥር ሾልከው ወይም ዘለው በመግባት የታሰረውን ውሻ ሊነክሱ እንደሚችሉ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ ውሾችን እንዳይዘዋወሩ አስሮ ማቆየት ብቻ ሳይሆን ክትባት እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የክትባት ዘመቻ፡ –
በአመት አንዴ ወይም ሁለት ጊዜ የውሾች ክትባት ዘመቻ መደረግ አለበት፡፡ በሽታውን ለመከላከል ከሚያስችሉ መንገዶች አንዱ ውሾችን ማስከተብ ሲሆን ውሻን የሚያሳድጉ ሁሉ ውሾቻቸውን ማስከተብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የተከተቡ ውሾችን ካልተከተቡ ውሾች ለመለየት በተከተቡ ውሾች አንገት ላይ የሚታሠር መለያ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፤ ይህንን ዘዴ ባለቤት ለሌላቸው ውሾችም መጠቀም ይቻላል፡፡
ባለቤት የሌላቸው የተልከስካሽ ውሾች ቁጥጥር፡ –
በሽታውን በማባዛት አይነተኛ ሚና የሚጫወቱት እነዚሁ ባለቤት የሌላቸው ውሾች ስለሆኑ የእነርሱን ቁጥር መቀነስ የበሽታውን ቁጥር መቀነስ ነው፡፡
የውሾች ምዝገባ፡ –
የውሾችም ቁጥር ያለመታወቅ ለውሾች ሊደረገላቸው የሚገባውን ክትትልና እንክብካቤ እንዲስተጓጎል አድርጓል፡፡ ከክትባት በኋላ ውሾችን መመዝገብ የውሾችን ቁጥር ለማወቅ ይጠቅማል፡፡ በአንዳንድ የበለፀጉ አገሮች ውሻን የሚያሳድጉ ሰዎች ለውሾቻቸው ታክስና የምዝገባ ክፍያ ሲጠየቁበት በሌሎች አገሮች ደግሞ ላልመከነች ሴት ውሻ ተጨማሪ የታክስ ክፍያ በመጠየቅ የውሾችን ቁጥር መጨመር ለመቆጣጠር ይረዳል፡፡
ሕብረተሰቡን ማስተማር፡ –
ሕብረተሰቡን ማስተማር የሚጠቅምበት ዋነኛው ምክንያት የበሽታውን ከውሻ በስተቀር ሌላ እንስሳ ሊለከፍ እንደሚችል ያለው ግንዛቤ በቂ ባለመሆኑ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ስለበሽታው ያላቸው ግንዛቤ የተዛባ ነው፤ ይህም አንዳንዱ የሕብረተሰቡ ክፍል ውሾችን ውሻን የሚያሳብደው በሽታ የሚይዛቸው ውሀ ሲጠማቸው ነው ብለው ሲያምኑ ሌሎች ደግሞ በእብድ ውሻ የተነከሰ ሰው ሆዱ ውስጥ ውሻ ይረባል ብለው ያምናሉ፡፡
ሕብረተሰቡ ይህን በሽታ በተመለከተ ያለው አስተሳሰብ ባህላዊ መንገድን የተከተለ በመሆኑ የሕብረተሰቡ ክፍል የችግሩ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፡፡ ስለዚህ የሕብረተሰቡን ስለበሽታው ማስተማርና ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ የሚድያዎች አስተዋፅኦ ከፍተኛ ድርሻ ይይዛል ሲል የኢትዮዽያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይገልፃል።
