
በመኮንን ተሾመ ቶሌራ
“የኢትዮጵያን የዶሮ እርባታና ልማትን የሚታደግ እርምጃ ነዉ።”

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ሀገራችን በህዝብ ብዛት በአፍሪካ ከናይጀሪያ ቀጥሎ ሁለተኛ ብትሆንም በነፍስ ወከፍ የዶሮ ሥጋ እና እንቁላል ፍጆታ በአለም ደረጃ በጣም ዝቅተኛ ቦታ ይዛ ትገኛለች። በሀገራችን አንድ ሰው በአማካይ በአመት 2.85 ኪሎ ግራም የዶሮ ስጋ እና 57 እንቁላል ብቻ ይጠቀማል።
ይህም በአለም ላይ በዶሮ ስጋ እና እንቁላል አጠቃቀም ከታዩ 165 ሀገራት ኢትዮጵያ 164ኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ እንዳደረጋት መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህም በጣም የሚያስቆጭ ጉዳይ መሆኑን ማንም አያጣዉም።
በኢትዮጵያ ብሄራዊ የዶሮ እርባታ ስትራቴጂ 2022–2031 ላይ እንደተጠሰሰዉ የዶሮ በሽታ፣ የአንድ ቀን ጫጩቶች አለመገኘት ፣ የገበያ አለመረጋጋት እና ደካማ መሆን ፣ እንዲሁም በቂ የክትባት አቅርቦት አለመኖርና የመሳሰሉት የኢትዮጵያ የዶሮ እርባታ እና አቅርቦት ማነቆዎች ሆነዉ ቆይተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በሀገራችን ዘመናዊ ዶሮ እርባታ ሳይንስና ምርምር አኳያም “የቅድመ ወላጅ (Grandparent)” ዶሮዎችንም ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ዉስጥ ነዉ የቆየነዉ።
የቅድመ ወላጅ ዶሮዎችን ማልማት እንደሃገር ያልቻልንባቸዉ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ዘመናዊና የተሻሻሉ ዶሮዎችን ጀኔቲክስ ደረጃዉን ጠብቆ ለማልማትና የባዮ ሴኪዩሪቲ ⁄ በልማቱ ሂደትም የባዮ ደህንነትን አስጠብቆ ለመሄድ ⁄ ከፍተኛ የሰው ሃይልና የዝርያ እጥረት መኖሩ በዋነኝነት የነበሩ ተግዳሮቶች ናቸዉ።
የሀገራችን የዶሮ ዝርያዎች በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ለመጣዉ የህዝባችን ቁጥር የዶሮ ስጋና እንቁላል ፍላጎት ለማሟላት ምርታማነታቸዉ በጣም ያነሰ ነዉ። ከዉጭ ሀገር የሚመጡ ዝርያዎች በዓመት እስከ 320 እንቁላሎች ይጥላሉ። ይህም የሀገራችን ዝርያዎች ከሚጥሉት በአማካይ ከአምስት እጥፍ በላይ ነው።
በመሆኑም እያደገ ያለዉን ፍላጎትና እጥረት ለመቅረፍ የተሻሻሉና የታወቁ ዝርያዎችን ማስመጣትና የዶሮ ልማቱን ማሳደግ አማራጭ የሌለዉ መሆኑ ከታመነበት አመታት ተቆጥረዋል።
የቅድመ ወላጅ ዶሮዎች ልማት
የዉጪ ዝርያዎች በማስመጣት ስራ ዉስጥ ደግሞ ለዝርያ ማራባትና ጥራት ወሳኝ የሆነዉ የቅድመ ወላጅ ዶሮዎች ልማት ነዉ። ምክንያቱም በዘመናዊ የዶሮ እርባታ ዉስጥ ለእንቁላልም ሆነ ለስጋ የሚሆኑ የወላጅ ዶሮዎችን በብዛት ለማምረት መሰረት የሚጥል በመሆኑ ነዉ።
የቅድመ ወላጅ ዶሮዎች ልማት ለዶሮ እርባታ ለስጋ እና ለእንቁላል ምርት የሚሸጠውን የመጨረሻውን ትውልድ ለማግኘት ወሳኝ ምንጭ ነዉ።
የቅድመ ወላጅ ዶሮዎች ልማት የዶሮ እርባታ ሰንሰለትን ውጤታማ ለማድረግ እና የጄኔቲክ ጥራትን ጠብቆ ምርታማነትን ለማረጋገጥ ያስችላል።

ከፍተኛ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም
እንደዚህ ያሉት ዘመናዊ የዶሮ እርባታዎች በጄኔቲክስ ጥበቃና ጥራት ላይ ያተኮረ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የዶሮ ዝርያዎች መረጣና ልማት የምርት ጥራቶችን ለማስጠበቅ ስለሚያስችል የገበያ ፍላጎቶችን እንዲያሟሉ ይረዳል። ይህም የኢንዱስትሪውን አጠቃላይ ቅልጥፍና እና ዘላቂነት ያለዉ እንዲሆን ያደርጋል።
በተጨማሪም የዶሮዎችን የምግብ ፍጆታ፣ የውሃ አጠቃቀምን እና የአካባቢ ሁኔታዎችን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎችን ለመከታተል እና ለማመቻቸት ሴንሰሮችን እና የአይቲ መሳሪያዎችን በመጠቀም የመረጃ ትንተናዎችን ይጠቀማል። ይህም የዶሮዎችን ደህንነትን ለማሻሻል ፣የእድገት ደረጃዎችን ለማሻሻል እና የግብአት ፍጆታን ለመቀነስ እንዲሁም ትክክለኛ ማስተካከያዎችን ለማድረግ ያስችላል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ትላንት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በሀዋሳ ከተማ አቅራቢያ ሻሎ እርሻ የሚገኘውን የኤልፎራ የዶሮ ልማት ማዕከል የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ፣ የግብርና ሚንስትር ዶ/ር ግርማ አመንቴ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ፣ አቶ ተክሉ ጃምባ የሲዳማ ክልል የእንስሳት ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ፣ በኢትዮጵያ የሀንጋሪ አምባሳደር አቲላ ታማሽ ኮፓኒ፣ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚዎች እንዲሁም አባ ገዳዎችና አደ ስንቄዎች በተገኙበት ተመርቋል።
ከኢንቨስትመንት ግሩፑ ማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ እንዳገኘነዉ መረጃ የግብርና ሚነስትሩ ዶ/ር ግርማ አመንቴ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ፕሮጀክቱን ያከናወነው ለትርፍ አለመሆኑንና የሀገር ኢኮኖሚን ለማሳደግ ትኩረት መስጠቱን በመግለፅ ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ጀማል አህመድና ድርጅታቸው ሚድሮክ ስለወሰዱት ቁርጠኝነት አመስግነዋል።
“ክቡር ሚኒስትሩ እንደ ሀገር የስጋ ተዋፅኦ ከውጭ በማስገባት ላይ የቆየን ሲሆን አሁን ላይ ሚድሮክ ፕሮጀክቱን በአስደናቂ ፍጥነት በማጠናቀቁና ችግሩን ለመፍታት የድርሻውን በመወጣቱ ደስታቸውን ገለፀዋል።አያይዘውም እንደ ሀገር በ2015 ዓ.ም 40 ሚሊዮን በ2016 ዓ.ም ደግሞ 80 ሚሊዮን ዶሮዎችን ማምረት መቻሉን ተናግረዋል።” ሲል ዘገባዉ አስታዉቋል።
ይህ ቁጥር ሃገሪቱ ካላት አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር አንፃር በቂ ባለመሆኑ መሰል ስርዓቶች መዘርጋታቸው ተገቢና ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ሚንስትሩ አስገንዘበዋል።
ይህን ቴክኖሎጂ በሀገራችን ማስጀመር ቀላል ስራ ባይሆንም በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ ቁርጠኝነት፤ በመላ አመራሩና ሰራተኛው ብርታት መሳካቱን ገልፀው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በወቅቱ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው ማዕከሉ ዘመናዊ የዶሮ እርባታ አሰራርን ባማከለ መልኩ በመዘጋጀቱ ገበያን ከማረጋጋት አንጻር ያለው ሚና ከፋተኛ መሆኑን ገልፀዋል።
ፕሮጅክቱ የዉጪ ምንዛሪን በማስቀረትና ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ ደህንነታቸው የተጠበቁ የዶሮ ግብዓቶችን እንዲያገኙ በማድረግ በኩል ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ተናገረዋል።
በተጨማሪ ኤልፎራ ለስጋና እንቁላል የሚያገለግሉ ዶሮዎችን በማቅረብ ላይ የሚገኝ ሲሆን አሁን ላይ ወላጅ ዶሮዎችን በብዛት በማምረት ከሀገር አልፎ ለሌሎች ሀገራትም ኤክስፖርት ለማደግ የሚያስችል አቅም እየፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የግብርና ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፈለቀ ታደሰ የተመረቀው ፕሮጀከት የማሕበረሰቡን በተለይም የአርሶ አደሩን ኑሮ ከማሻሻል አንፃር የላቀ ሚና ያለው መሆኑን ገልፅዋል።
አቶ ፈለቀ በምግብ ራስን መቻል ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው በዛሬው እለት የተመረቀው ፕሮጀክት በአንድ ዓመት ከ2 ወራት ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ በበኩላቸው ሚድሮክ ዛሬ ያስመረቀው ይህ ፕሮጀክት የነበረዉን የዶሮ አቅርቦት ችግር ከመፍታት ባሻገር ለዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር እንደሆነና እንደ ሀገር ለተያዘው የሌማት ቱሩፋት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል።
ሚድሮክ በልማት ብቻ ሳይሆን በድርቅ ጊዜም ከኦሮሚያና ከመላ ሀገራችን ህዝብ ጎን በመቆሙ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕን እና ሊቀ-መንበሩን ሼይክ መሀመድ ሁሴን አሊ አል-አላሙዲንን አመስግነዋል።
ፕሮጀክቱ በዘርፉ የሀንጋሪ እና የኢትዮጵያን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን በመገለጽ ሚድሮክ ከሀንጋሪ የግብርና ዘርፍ ባለሙያዎች ጋር በመስራቱና ሀገራቸውም የዚህ ታላቅ ታሪክ አካል በመሆኗ ደስታቸውን ገልጸዋል።
በ2017 ዓ.ም ከሌሎች ስራዎች በተጨማሪ ኤልፎራ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የቅድመ ወላጅ ዶሮዎች ስርዓትን ወደ ስራ በማስገባት እንደሀገር በአጠቃላይ 150 ሚሊዮን ዶሮዎችን በማምረት የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ዝግጅት መጠናቀቁን ተነግሯል ።
የቅድመ ወላጅ ዶሮዎች ልማት እና የባዮሴኪዩሪቲ
በቅድመ ወላጅ ዶሮዎች ልማት ዉስጥ ትኩረት ሊሰጠዉ የሚገባዉ የዶሮ እርባታ ሰንሰለትን ሊያበላሹ የሚችሉ በሽታዎች እንዳይከሰቱ እና እንዳይስፋፉ ለመከላከል የሚያስችሉ የባዮሴኪዩሪቲ ስራ ነው። ባለሞያዎች እንደሚሉተ ከሆነ ልማቱ ዘላቂ እንዲሆነ ከተፈለገ ጥብቅ የባዮሴኪዩሪቲ ፕሮቶኮሎችን አተገባበር ላይ አፅንዖት ሰቶ መስራት ያስፈልጋል። ይህም መደበኛ የጤና ክትትል እና የተሟላ የንፅህና አጠባበቅ ልምዶችን ያካትታል። በባዮሴኪዩሪቲ ቴክኖሎጂ ውስጥ ያሉ እድገቶች እንደ አውቶሜትድ ስርዓቶች በሽታዎችን ለመለየት እና ክትባቶችን መተግበር ያካትታሉ።
ይህም የጄኔቲክ ጥራትና ክምችትን መጠበቅና እንዲሁም የዶሮዎችን እና ሰራተኞችን ጤና እና ደህንነት መከታተል ይጨምራል። ባጠቃላይ የቅድመ ወላጅ ዶሮዎች ልማት ለዶሮ እርባታ ኢንዱስትሪ ስኬት ትልቅ ሚና ይጫወታል፣ ይህም ከፍተኛ ጥራት ያለው የወላጅ ክምችት ለማምረት መሰረት ሆኖ ያገለግላል። በዚህ ዘርፍ ውስጥ ያሉ የቅርብ ጊዜ አዝማሚያዎች፣ የዘረመል እድገቶች፣ የተሻሻሉ የባዮሴኪዩሪቲ እርምጃዎችና ዘላቂነት ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ነገር ግን እንደ ባለሞያዎች ከሆነ የተቀናጁ የበሽታ መቆጣጠሪያ አገልግሎቶችን መንደፍ እና መተግበር ፣ የክትትል እና የምርመራ አቅምን ማጠናከር ፣ ጥራት ያለው የመድሃኒት እና ክትባቶች አቅርቦትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ዞሮ ዞሮ አዲሱ የሚድሮክ የዶሮ እርባታ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምርቶች ለማግኘትና በአቀፍ ደረጃ ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ የሚያችል መሆኑ አያጠራጥርም።
በመሆኑም በዚህ ተስፋ ሰጪ ትልቅ ስራ ትልቁንና ተወዳጁን የሀገራችንን ኩባንያ ሚድሮክን እና ዋና ስራ አስፈፃሚዉን አቶ ጀማልን አለማመስገን አይቻልም !
