
በመኮንን ተሾመ (Opinion)
ሚትዎሮሎጂ
(አዲስ አበባ ፣ ኢትዮጵያ) – የሰዉ ልጅ ሳይንሳዊ ምርምሮችንና አሰራሮችን ማዳበር ከጀመረ ረጅም ጊዜ ሆኖታል ። ሳይንሳዊ የሆኑ ግኝቶችና ሀሳቦች በብዙ ማስረጃዎች የተመሰረቱ እና የተደገፉ በመሆናቸዉ እዉነታነታቸዉን መልሶ መልሶ ለማረጋገጥ የሚቻልባቸዉም አሰራሮች አሉ።
ሳይንሳዊ ነገሮች አዲስ ማስረጃ እና አመለካከቶች ከተገኙ ሊሻሻሉም የሚችሉበትም ሁኔታ ይኖራል።
በተቃራኒዉ ሳይንሳዊ ያልሆኑ ዘዴዎች ደግሞ በግለሰባዊ ልምድ ፣ በትውፊት ፣ በውስጣዊ ስሜት ፣ ሎጂክ እና ፣ ስልጣን ላይ ተመስርተዉ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ሊያደርጉን ይችላሉ። ሳይንሳዊ ያልሆኑ ግኝቶችና ሀሳቦች በማስረጃዎች የተመሰረቱ እና የተደገፉ ባለመሆናቸዉ እዉነታነታቸዉን መልሰን መሰን ለማረጋገጥ የሚያስችል አሰራሮች የሉም።

ይሁንና የሰዉ ልጆች ሳይንሳዊ አሰራሮች ከማደጋቸዉ በፊት በየሀገሩ በነበሩ የሀገር በቀል እዉቀቶችና አሰራሮች ሲጠቀሙ ኖረዋል።
በእርግጥ የሀገር በቀል ዕውቀቶች የማህበረሰቦች ችግሮች እንዲፈቱ፣ ባህላዊ ቅርሶች እንዲጠበቁ እና እንዲሁም ሰዎች በሰዎች እና በተፈጥሮ መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲገነዘቡ ይረዳሉ። የሀገር በቀል እውቀቶች የአንድ ማህበረሰብ የዘመናት የልምድና የህይወት ቅምሮች በመሆናቸው አስደናቂ የኑሮ ችግሮች መፍቻ መንገዶችም ሆነው ያገለግላሉ።
ይሁንና የሀገር በቀል ዕውቀቶች አሰራሮች ሳይንሳዊ ባለመሆናቸዉ ተደጋግመዉ ሊፈተሹና በሳይንሳዊ አሰራሮችም ሊደገፉ ይገባል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በአለም ዙሪያ በተለያዩ ማህበረሰቦች የአየር ሁኔታ ትንበያን ለማወቅ የሀገር በቀል እውቀትን መጠቀም የተለመደ ነዉ።እነዚህ የሀገር በቀል እውቀቶች ዘመናዊ ሳይንስ በሌለበት ሁኔታ እንደ አማራጭ የሚያገለግሉ ሲሆኑ እስተማማኝነታቸዉ ዝቅተኛ ስለሆነ በሳይንሳዊ ሰሰራሮች አየተደገፉ መሄዳቸው ይበልጥ ጠቃሚ ይሆናል።
የሜትሮሎጂ የአየር ሁኔታ ትንበያ ተደራሽነትና እዉቀት በሌለበት ሁኔታ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የተለያዩ የአየር ሁኔታን የመተንበያ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ ለምሳሌ የእንስሳት እና የነፍሳት ባህሪያትን መመልከት እና መተርጎም ፣የእንስሳት አንጀት ማንበብ፣ የኮከብ እና የጨረቃ ሁኔታን መመርመር ይገኙበታል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በምስራቅ አፍሪካ የኬንያና የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን ለአብነት መጥወስ ይቻላል።
ለምሳሌ በቅርብ አመታት ከተካሄዱ ጥናቶች መካከል በኢትዮጵያ የጉጂ አርብቶ አደሮች የድርቅን ሁኔታ ለመከታተል የሚጠቀሙበትን የአየር ሁኔታ ትንበያ አስመልክቶ “Indigenous weather forecasting among Gujii pastoralists in southern Ethiopia: Towards monitoring drought” በሚል የተሰራዉን ጥናት መመልከት ይቻላል።
እንደ ጥናቱ ከሆነ ምንም እንኳን የዘመናዊ የአየር ሁኔታ መረጃን ማግኘት እያደገ ቢሆንም ለጉጂ አርብቶ አደሮች እምብዛም ተደራሽ ሊሆን አልቻለም።
በዚህም ምክንያት አርብቶ አደሮቹ የተለያዩ የአየር ሁኔታ ክስተቶችን ለመተንበይ እና በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ለኑሮአቸው አገር በቅል እዉቀት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል።
በተለይም እንደ ድርቅ እና ውጤቶቹ ያሉ የአየር ንብረት አደጋዎችን ለመቋቋም አርብቶ አደሮቹ አገር በቅል እዉቀቶችን ይመርጣሉ ምክንያቱም በአጠቃቀም ሁኔታዉ ለነሱ ቀላል በመሆኑ ነዉ።
በአካባቢው ለወቅታዊ የአየር ሁኔታ ትንበያዎች ዘመናዊ ሳይንሰ የተደራሽነት ችግር በመኖሩ አገር በቅል እዉቀቶችን ይመርጣሉ። እንደ አርብቶ አደሮቹ ከሆነ አገር በቅል ዕውቀት የሚቲዎሮሎጂ መረጃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ በስፋት ጥቅም ላይ ይዉላል።
እንደ ጥናቱ ከሆነ እንደ ሀገር በቀል የአየር ሁኔታ ትንበያ የተለያዩ የእውቀት ምንጮችን ይጠቀማል። ሀገር በቀል ትንበያና የሜትሮሎጂ ትንበያ ስርዓቶችን ጎን ለጎን ማካሄድ በማህበረሰቦ አንድ ሳይናዊ የሜትሮሎጂ አሰራር ቀስ በቀስ ተቀባይነት እና እድገት እንዲያገኝ ስለሚረዳ ሁለቱንም አጣጥሞና አስማምቶ ወደ ተፈለገዉ ሳይነሳዊ ሽግግር ለመድረስ መሰራት እንዳለበት ባለድርሻ አካላት እና ፖሊሲ አውጪዎች ይስማማሉ።
በመሆኑም የሜትሮሎጂ ሳይንስ ባለሞያዎቻችን እና ሁሉም የሚመለከታቸዉ አካላት አሁን ያለንበትን ማህበረሰባዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት በመረዳትና አሳታፊ ሳይንሳዊ እድገት እንዲመጣ በማገዝ ሁሉም የማህበረሰባችን ክፍሎች የሳይንሳዊ የአየር ንብረት ትምበያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መስራት ይኖርባቸዋል።
ይህም ሀሳብ ሰሞኑን ሰሞኑን በአዲስ አበባ የኢጋድ የአየር ንብረት ትንበያ እና አፕሊኬሽን ማእከል የታላቁ የአፍሪካ ቀንድ የአየር ጠባይ ትንበያ እና የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ትላንት ጥር 17 ፣ 2017 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ባደረገዉ የበጋ ወቅት ትንበያ ግምገማና እንዲሁም ከካቲት እሰከ ግንቦት 2017 ዓ.ም. ያለዉን የበልግ ወቅት የአየር ጠባይ ትንበያ ይፋ በሆነበት ወቅት በተለያየ መልኩ የተነሳ ሀሳብ ነበር።
