
ስደተኞች
ከየመን ወደ ሳዑዲ ለመግባት በሞከሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የሳውዲ ድንበር ጠባቂዎች መትረየስ እና ሞርታር በመተኮስ በመቶዎች ምናልባትም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ሳይገድሉ እንዳልቀረ ሂዩማን ራይትስ ዎች ሰኞ ባወጣው ሪፖርት ላይ ገልጿል።
በተመሳሳይ ‘ሚክስድ ማይግሬሽን ሴንተር’ (MMC)] የተባለው ዓለም አቀፍ የፍልሰት ጥናት እና ትንተና መረብ ሐምሌ 5/2023 እ.ኤ.አ ያወጣውን አዲስ ጥናት መሠረት በማድረግ ድረ-ገጹ ባጠናቀረው ዘገባ ላይ “ሥራ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በስናይፐር እና በሞርታር ኢላማ ሆነዋል” ብሏል።
የግድያው ሰለባ የሆኑት ስደተኞች በኢኮኖሚ ችግር እና በጦርነት ሳቢያ ከአገራቸው በመፈናቀል ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ፣ ከዚያም በአደገኛ ሁኔታ በባሕር ወደ የመን፣ በመጨረሻም ወደ ሳዑዲ አረቢያ በየብስ ለመሻገር ሲሞክሩ በድንበር በጠባቂዎች እየተገደሉ መሆናቸውን የ‘ሚክስድ ማይግሬሽን ሰንተር’ መረጃ ያመለክታል።
ይህ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ተፈፀመ የተባለው ግድያ እና ጥቃት በየመን የሁቲ ታጣቂዎች በሚቆጣጠሩት አል-ጃውፍ በሚባል መስመር ሲሆን፣ ተመሳሳይ ጥቃቶችም በሳዑዲ አረቢያ ጂዛን ግዛት መፈጸማቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
እንደ ‘ሚክስድ ማይግሬሽን ሰንተር’ የተባለው ዓለም አቀፍ የፍልሰት ጥናት እና ትንተና መረብ ገለጻ እስካሁን ድረስ በግድያው እና በመብት ጥሰቶቹ ላይ ምንም አይነት ውጤታማ ምርመራ አለመካሄዱን አስታውቋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት እንዲሁም በሳዑዲ አረቢያ ጂዳ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
